ውፍረት ለመቀነስ የሚጥሩ ሰዎች እስከ 5 ዓመት ለልብና ስኳር ህመም የመጋለጥ እድላቸውን ይቀንሳሉ - ጥናት
ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም የተደረጉ 124 ጥናቶችን መሰረት አድርጎ ያደረገውን ጥናት ይፋ አድርጓል
በጥናቱ በስፖርት፣ በጾም፣ አመጋገብን በማስተካከልና የተለያዩ ክብደትን የሚቀንሱ እንክብሎችን የሚወስዱ 50 ሺህ ሰዎች ተሳትፈዋል
ጤናማ ያልሆነ የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ የሚደረጉ ጥርቶች ለልብ እና ስኳር ህመም ተጋላጭነትን በብዙ እጥፍ እንደሚቀንስ ተገለጸ።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ያልተስተካከለ ውፍረትን ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶች የጤና ፋይዳን በተመለከተ የተደረጉ ጥናቶችን መሰረት ያደረገ ምርምር አድርገዋል።
ጥናቶቹ በስፖርት፣ በጾም፣ አመጋገብን በማስተካከልና የተለያዩ ክብደትን የሚቀንሱ እንክብሎችን የሚወስዱ 50 ሺህ ሰዎችን ያሳተፉ ናቸው።
የጥናቱ ተሳታፊዎች ውፍረትን ለመቀነስ የሚያደርጉት ጥረት ውጤት ሲያሳይ በፍጥነት የማቆም ችግርን ይጋራሉ የሚሉት የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፥ በአማካይ 0 ነጥብ 32 ኪሎግራም ክብደት ጨምረው መገኘታቸውን ይገልጻሉ።
ያም ሆኖ ለረጅም ጊዜ ክብደት ለመቀነስ የተደረገ ጥረት ከተቋረጠ በኋላም የሚከተል የጤና በረከት እንዳለው አረጋግጠናል ብለዋል ተመራማሪዎቹ።
በተለይ የልብ እና ሁለተኛው አይነት የስኳር ህመምን ተጋላጭነት በመቀነስ ረገድ ውፍረት ለመቀነስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ጠንካራ የውፍረት መቀነስ ፕሮግራም ሲያደርጉ የቆዩ ሰዎች ካቋረጡት በኋላ ባሉት አምስት አመታት ለበሽታዎቹ የመጋለጥ እድላቸው መቀነሱንም ነው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ይፋ ያደረገው።
በአሜሪካ የልብ ማህበር ጆርናል ላይ የወጣው ጥናት ውፍረትን ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶች በቀይ የደም ህዋስ ውስጥ የሚገኘውን “ኤችቢኤ1ሲ” የተሰኘ ፕሮቲን መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል ይላል።
ይህም የስኳር ህመም ተጋላጭነትን እስከ 5 አመት ድረስ በ0 ነጥብ 26 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉን በጥናታችን አረጋግጠናል ብለዋል የጥናቱ ዋና ጸሃፊ ፕሮፌሰር ሱዛን ጄብ።
ጤናማ ያልሆነ ውፍረትን ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶች የደም ዝውውርን ጤናማ በማድረግ የልብና ተያያዥ ህመሞች ተጋላጭነትን ይቀንሳል የሚሉት ፕሮፌሰር ሱዛን፥
የተስተካከለ አቋምና ገጽታን ብቻ ሳይሆን ለአመታት የሚሸጋገር የጤና ስንቅን ለመያዝ በተለይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይገባል ማለታቸውንም ዴይሊ ሜል አስነብቧል።