ሰሜን ኮሪያውያን በኪም ጆንግ ኡን ውፍረት መቀነስ ተጨንቀው እያለቀሱ መሆኑ ተሰምቷል
ከመሪው የሰውነት ውፍረት መቀነስ ጀርባ የውጭ ሀገራት እጅ ሊኖር ይችላል- የሀገሪቱ ዜጎች
የሀገሪቱ ህዝብ ለመሪው ያለውን እምነት እንዲጨምር የተሰራ የፖለቲካ ጨዋታ ነው- የፖለቲካ ተንታኞች
ሰሜን ኮሪያውያን የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ውፍረት መቀነስ በእጅጉ መጨነቃቸውና እያለቀሱ መሆኑ ተሰምቷል።
የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ ሚዲያ የሀገሪቱን ዜጎች አነጋግሮ በሰራው ዘገባ ከመሪያቸው የሰውነት ውፍረት መቀነስ ጀርባ የውጭ ሀገራት እጅ ሊኖር ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው ገልጿል።
“ኪም ጆንግ ኡን በዚህ መልኩ ሰውነታቸው ከስቶ መታየቱ ልባችንን ሰብሯል” ያሉት ነዋሪዎቹ፤ “ሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ የኪም ጆንግ ኡን ጤንነት አሳስቦት እያነባ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
በቅርብ ጊዜ ይፋ የተደረገ ፎቶግራፍ እንደሚያመለክተው 1 ሜትር ከ70 ሳንቲ ሜትር ቁመት ያላቸው ኪም ጆንግ ኡን የተወሰነ ክብደት ቀንሰዋል።
ከዚህ ቀደም 140 ኪሎ ግራም የሰውነት ክብደት እንዳላቸው የሚነገረው መሪው፤ በቅርብ ጊዜያት ከ10 እስከ 20 ኪሎ ግራም መቀነሳቸው እንዳልቀረ ነው የተነገረው።
የሰሜን ኮሪያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች፤ የሀገሪቱ ህዝብ ለመሪው ኪም ጆንግ ኡን ያለውን እምነት እንዲጨምር ለማድረግ በማሰብ የሰውነታቸው ውፍረት መቀነስ አጀንዳ ሳይደረግ እንዳልቀረ ይናገራሉ።
“ሀገሪቱ የገጠማትን የምግብ እጥረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለመቅረፍ ኪም ምግብ ሁላ ሳይበሉ እና ቀን ከሌት በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ እየሰሩ ነው ክብደታቸው የቀነሰው” የሚል የፖለቲካ ጨዋታ ይዘት ያለው መልእክት የማስተላለፍ አላማ እንዳለውም ተንታኞቹ ገምተዋል።
ኪም ጆንግ ኡን ታመውም ይሁን በራሳቸው ፍላጎት የሰውነታቸውን ክብደት ቢቀንሱም የሀገሪቱ ቴልቪዥን ጉዳዩን ለምን አጀንዳ አደረገ የሚለው ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም ተብሏል።
ከዚህ ቀደምም ኪም ጆንግ ኡን በፈረንጆቹ 2014 ለ40 ቀናት ያክል ከህዝብ እይታ ጠፍተው መክረማቸውን ተከትሎ ታመው አሊያም ሞተው ነው ተብሎ ተወርቶ እንደነበረም ይታወሳል።
ኪም ጆንግ ኡን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከህዳር 2011 ጀምሮ የሀገሪቱ መሪነት ስፍራን ከአባታቸው ኪም ጆንግ ኢል ተረክበው ሰሜን ኮሪያን መምራት የጀመሩ ሲሆን፤ አhuን ያሳዩት የሰውነት ክብደት መቀነስ በባለፉት 10 ዓመታ ውስጥ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
ኪም ጆንግ ኡን ሰሜን ኮሪያን የመሩ ሶስተኛው ትውልድ የኪም ቤተሰብ ሲሆኑ፤ ወደ ፊት ኪምን ማን ሊተካ ይችላል የሚለው የብዙሃን ጥያቄ ነው።