ኢትዮጵያ 2 ሺህ ሙሽሮችን በሚሊኒየም አዳራሽ ዳረች
ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡት ሙሽሮች የቀለበት ስነ ስርአት በማድረግ ጋብቻቸውን ፈፅመዋል
የሺህ ጋብቻ ካርኒቫልና ኤክስፖ 2016 1 ሺህ ጥንዶች በጋራ ተሞሽረውበታል
2 ሺህ ሙሽሮች በዛሬው እለት በሚሊኒየም አዳራሽ በጋራ ተሞሽረዋል።
ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ 1 ሺህ ጥንዶች ናቸው ቀለበት አስረው በይፋ ጋብቻቸውን የፈጸሙት።
ግዙፉን የቡድን ሰርግ ያዘጋጁት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና ያሜንት ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ናቸው።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ማህበረሰብ ያለ ቤተሰብ መቆም እንደማይችልና ትዳር የተረጋጋ ማህበረሰብ መፍጠሪያ ትልቅ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
የሺህ ጋብቻ ካርኒቫልና ኤክስፖ-2016 በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ 2 ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝን ዳቦ እንዲሁም 20 ሜትር ርዝመት ያለው ኬክ ቀርቦ በሙሽሮች መቆረሱ ተገልጿል።
በሰርግ ስነ-ስርአቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ አምባሳደሮች የተገኙ ሲሆን የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋብቻቸውን ለፈፀሙ ጥንዶች ትዳራቸው የተባረከና ያማረ እንዲሆን መርቀዋል ተብሏል።