በጋራ የተሞሸሩት አፍጋኒስታናውያን የአመታት የተናጠል ምኞታችን በህብረት አሳክተነዋል ብለዋል
በአፍጋኒስታን 50 ጥንዶች በአንድ አዳራሽ የተሞሸሩበት የሰርግ ስነስርአት ከሰሞኑ ተካሂዷል።
በካቡል የተካሄደውን የጋብቻ ስነስርአት ለአዲስ ተጋቢዎች ምንጣፍና ሌሎች የቤት ቁሳቁሶችን የሚሰጥ በጎ ሰናይ ድርጅት አዘጋጅቶታል ተብሏል።
በሁለት አስርት አመታት ጦርነት ኢኮኖሚዋ ክፉኛ በተጎዳባትና የኑሮ ውድነቱም በጨመረባት አፍጋኒስታን በተናጠል ሰርግ መደገስ ከባድ ከሆነ ሰነባብቷል።
በመሆኑም ሰርግ ለመደገስ አቅም ያነሳቸው ሰዎች ከሌሎች ቢጤዎቻቸው ጋር በመቀናጀት ወጪ የሚቀንስ የጋራ ሰርግ ማዘጋጀት እየተለመደ መጥቷል ይላል የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ።
ሮሁላህ ሬዛይ የተባለ ሙሽራ እንደሚለው በአፍጋኒስታን ባህልና ወጉን የጠበቀ ሰርግ ለመደገስ ከ200 እስከ 250 ሺህ የሀገሪቱን ገንዘብ (ከ2 ሺህ 800 እስከ 360 የአሜሪካ ዶላር) ያስወጣል።
በካቡል ከ49 መሰሎቹ ጋር ሲሞሸር ግን ወጪው ከ15 ሺህ አፍጋኒስ (የሀገሪቱ ገንዘብ) እንዳልበለጠም ነው የተናገረው።
“በሰርጋችን ላይ 35 ቤተሰቦቻችን ጠርተናል፤ በየግላችን ደግሰን ቢሆን ከ300 እስከ 400 ሰው እንጠራ ነበር” የሚለው ሬዛይ፥ ወጪ ቀናሹን የህብረት ሰርግ ያዘጋጁ አካላት ውለታቸው አለብኝ ሲል ተናግሯል።
“ይህቺን ቀን ላለፉት ሶስት ቀናት ስጠብቃት ነበር” የሚለው የ23 አመቱ ሙሽራ ሳሚላህ ዛናሚም፥ መሰል የጋራ ሰርጎች ካልተደረጉ በትዳር መተሳሰር የሚፈልጉ በርካታ ጥንዶች አመታትን ለመጠበቅ ይገደዳሉ ባይ ነው።
ታሊባን በ2021 ዳግም ወደ ስልጣን ከተመለሰ በኋላ ሙዚቃና ዳንስ በመከልከሉ የካቡሉ ግዙፍ ሰርግ ዝምታ ውጦት ነበር ተብሏል።
ከቅዱስ ቁርአን ስለጋብቻ ክቡርነት የሚያወሱ ጥቅሶች ተነበው ምሳ ከተበላ በኋላ ሙሽሮች በተዘጋጁላቸው መኪኖች ከውሃ አጣጮቻቸው ጋር ለሽርሽር ወጥተዋል።