ዶናልድ ትራምፕ ቭላድሚር ፑቲንን “በጆ ባይደን ጉዳይ ውለታ ዋልልኝ” ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ ሀንተር ባይድን በሩሲያ ሚስጥራዊ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳለው ይነገራል
ትራምፕ፤ ፑቲን ስለ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሚያውቁትን “አደገኛ” ሚስጥሮች ይፋ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል
የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያው ፕሬዝንት ቭላድሚር ፑቲንን፤ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዙሪያ ውለታ እንዲውሉላቸው መጠየቃቸው ተሰምቷል።
በትናትነው እለት በተለቀቀ ቃለ መጠይቅ ላይ የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የሩሲያው ፕሬዝንት ቭላድሚር ፑቲን የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ሊጎዳ የሚችል በእጃቸው ላይ የሚገኝ መረጃን ይፋ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ከጀስት ዘኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ ሀንተር ባይድን በሩሲያ በድብቅ ስላለው ሚስጥራዊ የንግድ ስምምነት አንስተዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ያላቸውን ማንኛውንም መረጃ ይፋ እንዲያደርጉም ነው ትራምፕ የጠየቁት።
ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ ሀንተር ባይድን በሩሲያ በድብቅ ያለውን ንግድ አንስተው፤ “ፑቲን መልሱን በደንብ ያውቃል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።
“ፑቲን ስለ ሚስጥራዊው ንግድ ያለውን መረጃ ይፋ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ፤ ያኔ ምን እንደሆነ ሁላችሁም ታውቃላችሁ” ሲሉም ተናግረዋል።
የአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ የትራምፕ የተናገሩት ነገር የሀገር ውስጥ ፍላጎታቸውን በአሜሪካ ዋነኛው ጠላት በኩል ለማሳከት የተደረገ ሙከራ ነው ተችሏል።
ዶናልድ ትራምፕ የሀገር ውስጥ ፍላጎታቸውን ለማሟላት በዩክሬን ያለውን ጦርነት እየመሩ ያሉትን ፑቲንን ጨምሮ የውጭ ኃይሎችን ከመለመን እና ከመጠቀም ወደ ኋላ እንደማይሉ ያሳያልም ብሏል የቴሌቪዥን ጣቢያ ዶናልድ ትራምፕን በተቸበት አስተያየቱ።
ሀንተር ባይደን አባቱ ጆ ባይደን የአሜሪካ ምክትል ፐሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜ ለሚሰራው የማማከር ስራ እንደ ዩክሬን እና ቻይና ካሉ ሀገራት ገንዘብ ይቀበል እንደነበረ ይነገራል።
የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ በገንዘብ ዝውውሩ ዙሪያ የወንጀል ምርመራ እያደረገ ሲሆን፤ ባይደነ የአሜሪካን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሚጎዳ የሙስና ተግባር ላይ ስለመሳተፋቸው አስካሁን የተገኘ መረጃ የለም።
አሁን እየተካሄደ ያለው የወንጀለ ምርመራም ከፐሬዚዳንት ባይደን ጋር ግንኙነት የሌለው እና በልጃቸው ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሲሆን፤ ሀንተር ባይደን ግን “ምንመ ጥፋት አልሰራሁም” ሲል ቃሉን ሰጥቷል።