ዶናልድ ትራምፕ “ጆ-ባይደን አሜሪካን እያዋረዳት ስለሆነ በ2024 ድጋሚ ለምርጫ ልወዳደር እችላለሁ” አሉ
ትራምፕ “በ2024፣ ከሁሉም በላይ፣ ቆንጆ፣ የሆነውን ዋይት ሀውስን እንመልሰዋለን" ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል
አሜሪካ ምንም በማያውቅ ፕሬዝዳንት በመመራት ላይ ናትም ብለዋል ዶናልድ ትራምፕ
የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ “ጆ-ባይደን አሜሪካን እያዋረዳት ስለሆነ በ2024 ድጋሚ ለምርጫ ልወዳደር እችላለሁ” በማለት ፍንጭ ሰጡ።
ትራምፕ ይህን ያሉት በኖርዝ ካሮላይናዋ፤ ሴልማ ከተማ በትናንትናው እለት በተካሄደውና በርካታ ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት የ“ሴቭ አሜሪካ (አሜሪካን እናድን)” ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ነው።
“ልጆቻችን ኢንዶክትሪን እየተደረጉ፣ እሴቶቻችን እየተራከሱ ፣ ቅርሶቻችን እየጠፉ እንዲሁም ሀገራችን እየተዋረደች ያለችው ምን እየተካሄደ እንዳለ በማያውቅ ፕሬዝዳንት ምክንያት ነው” ሲሉም ዶናልድ ትራምፕ ተደምጠዋል።
አወዛጋቢው አሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጪው ምርጫ የመወዳደር እቅድ እንዳላቸውም በመርሃ ግብሩ ላይ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር፤ "ከመጀመሪያው በበለጠ በሁለተኛ ጊዜ በጣም የተሻለ ነገር እሰራለሁ፤ እናም ይህንን ማድረግ አለብን፤ እኔን ለሁለተኛ ጊዜ ስወዳደር ማየት ሚፈልግ ሰው አለ ?” የሚል ጥያቄም አቅርበዋል።
በህዳር ወር ስለሚካሄደው የዘመን አጋማሽ ምርጫ የጠቀሱት ትራምፕ : “ዓመቱ ቤቱን የምንመልስበት ዓመት ነው”ም ብለዋል ።
“ሴኔትን እንመልሳለን፣ አሜሪካን እንመልሳለን፣ እንዲሁም በ2024፣ ከሁሉም በላይ፣ ቆንጆ፣ ቆንጆ እና ቆንጆ የሆነውን ዋይት ሀውስን እንመልሰዋለን" ሲሉም ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።
ትራምፕ እንደፈረንጆቹ በ2016 የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተንን በማሸነፍ ተመረጡበት ሂደት ያልተጠበቃና በርካቶችን ያስደነገጠ እንደነበር አይዘነጋም።
እንደፈርነጆቹ በ2020 በአሜሪካ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ጆ-ባይደን ድል ቢቀዳጁም አወዛጋቢው ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለታቸው ደጋፊዎቻቸው በርካታ ድርጊቶች ሲፈጽሙ እንደነበር ይታወሳል።
ደጋፊዎቻቸው በተለይም በዋሽንግተን የሚገኘውን የካፒቶል ህንፃ የወረሩበት ክስተት፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዴሞክራሲ ረዥም ርቀት ተጉዛለች በምትባለው ሀገረ አሜሪካ ይሆናል ብሎ ያልጠበቀው ትልቅ ግርምት የፈጠረ አጋጠሚ ነበር።