ዶናልድ ትራምፕ እና ልጆቻቸው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የኒውዮርክ ፍርድ ቤት ወሰነ
በትራምፕ የሚተዳደረው ተቋም የመንግስት ብድር ለማግኘት በሚል "ያልተገባ ሃብት" አስመዝግቧል በሚል ተከሷል
ዶናልድ ትራምፕ ክሱ ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገበ የማይረባ ነው ሲሉ አጣጥለውታል
ትራምፕ እና ልጆቻቸው ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የኒውዮርክ ፍርድ ቤት መወሰኑ ተገልጿል፡፡
ትራምፕ እና ልጆቻቸው ኒውዮርክ ወደ ሚገኘው ፍርድ ቤት የሚቀርቡት ቃለ መኃላ በመፈጸም ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
የኒውዮርክ አቃቤ ህግ ዶናልድ ትራምፕ የሚያስተዳድሩትን ተቋም የግብር እና ብድር እፎይታ ለማግኘት በሚል " የሚያሳስት እና ያልተገባ የንብረት ግምገማ" በማድረግ አጭበርብረዋል ሲል መክሰሱ የሚታወቅ ነው፡፡
በዚህም ዶናልድ ትራምፕ በ21 ቀናት ውስጥ ወደ ፍርድቤት ቀርበው ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ የኒውዮርክ ፍርድ ቤት ዳኛ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የዳኛውን ውሳኔ ተከትሎ የዶናልድ ትራምፕ ተቋም ለቢቢሲ በላከው ምላሽ "አሰራሩ በሙሉ የተባለሸ ነው" በማለት ለቀረበለት ክስ ያለውን ተቃወሞ ገልጿል፡፡
ይሁን እንጅ በትናንትናው እለት ዶናልድ ትራምፕ፣ ወንድ ልጃቸው ትራምፕ እና ሴት ልጃቸው ኢቫንካን የፍርድ ቤትን ትእዛዝ ሊያከብሩ እንደሚገባ የኒውዮርክ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አርተር ኢንጎሮ ተናግሯል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የተጀመረው የፍርድ ሂደት ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገበ የማይረባ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
ትራምፕ የፍርድ ሂደቱን ቢያጣጥሉትም የፍርድ ቤት ትእዛዝ ያከብራሉ ወይስ አያከብሩም ለሚለው እስካሁን ግልጽ ያደረጉት ነገር የለም፡፡
ጠበቆቻቸውም ቢሆኑ ዶናልድ ትራምብ በፍርድ ቤት ሂደት ባለ ጉዳይ ላይ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠቡ የሚል ምክር እያቀረቡላቸው ነው፡፡
እንደፈረንጆቹ በ2019 የጀመረው የዶናልድ ትራምፕ ክስ ተቋማቸው ከመንግስት የሚያገኘውን ብድር ከፍ ለማድረግ የተጋነነ ሃብት አስመዝግቧል የሚል እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡