የ2024 ምርጥ 10 የአፍሪካ አየር መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተከታታይ 7ኛ ጊዜ የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ተብሎ ተመርጧል
ስካይትራክስ በመንገደኞች ምርጫ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገዶችን ዝርዝረ ይፋ አድርጓል
በዓለም አቀፍ ደረጃ አየር መንገዶችን የሚገመግመው ስካይትራክስ ድርጅት የዓለም 100 ምርጥ አየር መንገዶችን ዝርዝር በቅርቡ ይፋ አድርጓል።
በዘንድሮው የስካይትራክስ ዝርዝር በተለይም የአፍሪካ አየር መንገዶች አስደናቂ አፈጻጸም አሳይተዋል።
የመንገደኞች ምርጫ በሚል በተሰየመው የስካይትራክስ ሽልማጽ ከፈረንጆቹ 2023 እስከ 2024 በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ከ325 በላይ አየር መንገዶች ተገምግመዋል።
ከመስከረም 2023 እስከ ግንቦት 2024 በተሰበሰበው የመንገደኞች አስተያየት መጠይቅ ላይም ከ100 ሀገራት የተውጣቱ ሰዎች መሳተፋቸውም ነው የተገለጸው።
በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2024 የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ሽልማትን ያሸነፈ ሲሆን፤ አየር መንገዱ ሽልማቱን ለተከታታይ 7ኛ ዓመት መሸነፍ ችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም አየር መንገዱ የአፍሪካ ምርጥ ቢዝነስ ክላስ እና ኢኮኖሚክ ክላስ እንዲሁም በአፍሪካ ለኢኮኖሚ ክላስ ተጓዦች ምርጥ የበረራ ላይ ምግብና መጠጥ አቅራቢነት በጥቅሉ አራት ሽልማቶችን አግኝቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው "የ2024 የዓለም አየር መንገድ ሽልማትን ለሰባተኛ ተከታታይ ዓመት በማግኘታችን ደስተኛ ነን ያሉ ሲሆን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞችን ያማከለ አዲስ ፈጠራ ለመተግበር ያለን ቁርጠኝነት ለስኬታችን ወሳኝ ነበር ብለዋል።
በስካይትራክስ መረጃ መሰረት የአፍሪካ ምርጥ 10 አየር መንገዶች እንደሚከተለው ቀርበዋል
1ኛ የኢትዮጵያ አየር መንገድ (ኢትዮጵያ)
2ኛ ሮያል ኤር ሞሮኮ (ሞሮኮ)
3ኛ የደቡብ አፍሪካ አየር መንግድ (ደቡብ አፍሪካ)
4ኛ የኬንያ አየር መንገድ (ኬንያ)
5ኛ ሩዋንዳ ኤር (ሩዋንዳ)
6ኛ ኤር ሞሪሽየስ (ሞሪታኒያ)
7ኛ ኢጂፕት ኤር (ግብጽ)
8ኛ ኤርሊንክ (ደቡብ አፍሪካ)
9ኛ ሊፍት ኤርላይንስ (ደቡብ አፍሪካ)
10ኛ ፍላይ ሴፍኤር ((ደቡብ አፍሪካ)