የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ 67 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ተስማማ
አየር መንገዱ ከቦይንግ ጋር ስምምነቱን የተፈራረመው በዱባይ እየተካሄደ ከሚገኘው የ2023 የአየር ትርኢት ጎን ለጎን ነው
ቦይንግ ከአፍሪካ ሀገራት በርካታ የአውሮፕላን ግዥ ሲቀርብለት ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአሜሪካው ቦይንግ ኩባንያ 67 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ተስማምቷል።
አየርመንገዱ 11 “787” ድሪምላይነር እና 20 “737 ማክስ” አውሮፕላኖችን ለመግዛት እና 36 መሰል አውሮፕላኖችን በቀጣይ ለማዘዝ ነው የተስማማው።
በዱባይ እየተካሄደ ከሚገኘው የ2023 የአየር ትርኢት ጎን ለጎን የተፈረመው ስምምነት የአየር መንገዱን የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ቁጥር 50 ያደርሰዋል ተብሏል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2035 ራዕዩን ለማሳካት እንደሚያግዝ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል።
የቦይንግ “787 ድሪምላይነር እና “737 ማክስ” አውሮፕላኖች ግዥ ትዕዛዙ አየር መንገዱ የአየር ብክለትን ለመቀነስ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ያሳያልም ነው ያሉት።
የቦይንግ የሽያጭ እና ማርኬቲንግ ምክትል ፕሬዝዳንት ብራድ ማክሙለን በበኩላቸው፥ የአውሮፕላን ግዥ ስምምነቱ የኢትዮጵያ አየርመንገድ በአፍሪካ ቀዳሚነቱን ለማስቀጠል ያለውን ትልም ያሳያል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ከቦይንግ ጋር ለ75 አመታት የዘለቀ አጋርነት እንዳለው በመጥቀስም የ”787 ድሪምላይነር” አውሮፕላኖችን በመጠቀም ከአፍሪካ ቀዳሚው አየርመንገድ መሆኑን አውስተዋል።
አየር መንገዱ ያዘዘው “787-9” ድሪምላይነር አውሮፕላን የነዳጅ ፍጆታው እና የብክለት መጠኑ ከቀደሙት አውሮፕላኖች በ25 በመቶ እንደሚቀንስ ተገልጿል።
“737-8” የተሰኘው የማክስ አውሮፕላን ሞዴልም የነዳጅ ፍጆታና ብክለትን በ20 በመቶ እንደሚቀንስ ነው አየርመንገዱ በድረገጹ ላይ ያሰፈረው።
80 የቦይንግ አውሮፕላኖች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያዘዛቸው 30 “737 ማክስ” አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፥ የዛሬው ስምምነት የ“737 ማክስ” አውሮፕላኖቹን ቁጥር ወደ 50 ያሳድጉለታል።
ዛሬ በዱባይ የተፈረመው የአውሮፕላን ግዥ ስምምነት ቦይንግ በታሪኩ ከአፍሪካ ከቀረቡለት የግዥ ጥያቄዎች ሁሉ ቀዳሚው ነው ተብሏል።