በአሚሶም ተልዕኮ ስር የነበሩ ከ10 በላይ የኬንያ ወታደሮች ተገደሉ
ኬንያ በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ጦር ካዋጡ አገራት መካከል አንዷ ናት
ግድያውን የፈጸሙት አሸባሪው የአልቃይዳ ታጣቂዎች ናቸው ተብሏል
በአሚሶም ተልዕኮ ስር የነበሩ ከ10 በላይ የኬንያ ወታደሮች ተገደሉ፡፡
በጎረቤት አገር ሶማሊያ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የአፍሪካ ህብረት ከተመድ የሰላም ማስከበር ተቋም እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር ነበር የሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ሞቃዲሾ እንዲላክ የወሰነው፡፡
በዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሰላም አስከባሪ ጦር እንዲያዋጡ በማድረግ በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ወይም አሚሶም የተሰኘ ጦር ወደ አገሪቱ ከላከ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
አሚሶም ሶማሊያ አንጻራዊ ሰላም እንድታገኝ እና የአገሪቱ የጸጥታ መዋቅር እንዲደራጅ በማድረግ በኩል ውጤታማ ስራዎችን ቢያከናውንም አልቃይዳ የተሰኘው የሽብር ቡድን ግን ጥቃቱን ሊያቆም አልቻለም፡፡
ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ በአሚሶም ስር ወደ መቋዲሾ ከተሰማራው ጦር መካከል አንዱ የሆነው የኬንያ ሰላም አስከባሪ ጦር አባላት የሆኑ ከ10 በላይ ወታደሮች በሽብር ቡድኑ መገደላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በኬንያ እና ሶማሊያ ድንበር አቅራቢያ ሰፍሮ የነበረው የኬንያ ጦር ጌዶ ክልል ላይ በአልቃይዳ ታጣቂዎች እንደተገደሉም ተገልጿል፡፡
ከሞቱት በተጨማሪም አምስት ወታደሮች መቁሰላቸውን ያከለው ዘገባው አደጋው የሽብር ቡድኑ ተሽከርካሪ ላይ በተገጠመ መሳሪያ መድረሱ ተጠቅሷል፡፡
ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ለማድረግ በውዝግብ ላይ ያለችው ሶማሊያ የደህንነት ሁኔታው አሁንም ፈተና የሆነባት ሲሆን አልቃይዳን ለማዳከም አሜሪካ በሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች የታገዘ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናት፡፡
የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ ቀስ በቀስ በሶማሊያ ያሰማራቸውን ሰላም አስከባሪ የጦር አባላት ቁጥር የመቀነስ እቅድ እንዳለው በቅርቡ አስታውቋል፡፡
ሶማሊያ በአልቃይዳ ከሚሰነዘርባት የሽብር ድርጊት በተጨማሪ ባለፉት አርባ አመታት ውስጥ ያልተከሰተ ከባድ ድርቅ ተከስቶ ለ7 ሚሊዮን ዜጎቿ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንዲደረግላት ጠይቃለች፡፡