በኬንያ በማታቱ የህዝብ ማመላለሻ መኪና ላይ በቦምብ በተፈፀመ ጥቃጥ በትንሹ የ10 ሰዎች ህይወት አለፈ
ፖሊስ ጥቃቱ በኬንያ-ሶማሊያ ድንበር በሚንቀሳቀሱት የአልሸባብ ታጣቂዎች የተቀነባበረ ነው ብሏል
ከጥቃቱ በፊት ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ሆላንድንና የተለያዩ የምዕራባውያን መንግስታት ማስጠንቀቅያ ሲሰጡ ነበር
በኬንያ አረብ-ማንዴራ አውራ ጎዳና፤ ማታ የሚል መጠሪያ ባለው የህዝብ ማመላለሻ ላይ በቦምብ በተፈፀመ ጥቃት በትንሹ የ10 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል።
ማታቱ በተሰኘ መካከለኛ የህዝብ ማመላለሻ ላይ ባጋጠመው ፍንዳታ ምክንያት በርካታ ተሳፋሪዎች ኩፉኛ መጎዳታቸውንና መቁሰላቸውንም ሲጂቲኤን አፍሪካ የአይን እማኞች ነግረውኛል ብሏል በዘገባው።
የኬንያ ፖሊስ በበኩሉ በአደጋው ቢያንስ ስምንት ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ተናግሯል።
ፍንዳታውን በኬንያ-ሶማሊያ ድንበር ዘልቀው በገቡና በድንበሩ አካባቢ በሚንቀሳቀሱት የአልሸባብ ታጣቂዎች የተቀነባበረ እንደሆነም ነው ፖሊስ የገለጸው።
የሰሜን ምስራቅ ግዘት አዛዥ ጆርጅ ሴዳ ከቦምብ ፍንዳታው ጀርባ ያሉትን ለማሳደድና በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ፈረንሳይ፣ አሜሪካ እና ሆላንድን ጨምሮ የተለያዩ የምዕራባውያን መንግስታት የሽብር ጥቃት ሊፈፀም ይችላል የሚሉ ማስጠንቀቅያ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።
የውጭ መንግስታት ማስጠንቀቅያ ቢሰጡም በኬንያ በኩል መሰል ጥቃቶችን ለመከላከል ሲደረግ የነበረው ዝግጅት እምብዛም አልነበረም ተብሏል።
የአልሸባብ አሸባሪዎች በግዘቱ በሚገኙ ቦታዎች በተለይም በማንዴራ እና ጋሪሳ አውራጃዎች የጸጥታ ቀጠናዎችን ጥሰው በመግባት ጥቃት ሲሰነዝሩ የቆዩ ሲሆን፤ በዚህም በደርዘን የሚቆጠሩ ንፁሀን ዜጎች እና የጸጥታ ባለስልጣናት ሞተዋል እንዲሁም ቆስለዋል።
አሸባሪዎች በአከባቢው የሚሰነዝሩት ጥቃት አሁንም ድረስ አስጊ በመሆኑ፤ በአከባቢው የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል።