አሚሶም በሞቃዲሾ የተፈጸመውን “የፈሪዎች ጥቃት በፅኑ አወግዛለሁ” አለ
በሞቃዲሾ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ የ8 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ 17 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሶማሊያ ህዝብና መንግስት ጎን እንደሚቆምም አሚሶም አረጋግጧል
የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሚሶም) በትናንትናው እለት ጠዋት በሞቃዲሾ የደረሰውን ጥቃት አወገዘ።
የአሚሶም ኃላፊ አምባሳደር ፍራንሲስኮ ማዴይራ፤“የእለት ተእለት ስራቸውን ሲያከናውኑ በነበሩ ንፁሀን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን የፈሪዎች ጥቃት በፅኑ እናወግዛለን፤ ይህ አልሸባብ ለሰው ሕይወት ያለውን ንቀት የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ ነው” ብለዋል።
አሚሶም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሶማሊያ ህዝብና መንግስት ጎን በመቆም በሀገሪቱ ሰላም ለማምጣት እና ህይወትን መደበኛ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት አምባሳደሩ።
አምባሳደር ማዴይራ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ለተጎዱት ደግሞ ፈጣን ማገገምን ተመኝቷል፡፡
በሆዳን አውራጃ አንድ ትምህርት ቤት አካባቢ በተሽከርካሪ ላይ የተቃጠለ ፈንጂ ፈንድቶ ተማሪዎችን፣ ሌሎች ንጹሃን ዜጎችን መግደሉን እና ንብረት ማውደሙ ይታወቃል።
ጥቃቱን ተከትሎ አልሻባብ ጥቃቱ በተፈፀመበት ቦታ የአሚሶም ንብረት እና ሰራተኛ ነበረ ቢልም፤ ምንም አይነት የአሚሶም ኮንቮይ እንዳልነበረ አሚሶም አስታውቋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ፍንዳታው ያነጣጠረው የግል የደህንነት ድርጅት ነበርም ነው የተባለው።
በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ሌሊት ላይ በደረሰው ፍንዳታ ከፍተኛ የፍንዳታ አደጋ ቢያንስ የ8 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ 17 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል።
ሮይተርስ እማኙን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ፍንዳታው ከደረሰበት ቦታ ላይ የጭስ ይታይ ነበር እንደሁም የጥይት ድምጽ ሲሰማ ነበር ብሏል።
ሰኞ እለት የሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎች በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል የታችኛው ሸበሌ ጠቅላይ ግዛት አፍጎዬ አከባቢ በአሸባሪው የአልሸባብ እንቅስቃሴ ላይ ልዩ ዘመቻ መፈጸሙ የሚታወስ ነው።
በዘመቻው የኦፊሴላዊው የሰራዊት ድምጽ ራዲዮ የስለላ አገልግሎቱ፤ ሶስት የአልሸባብ ንቅናቄ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ማስታወቁም ጭምር ይታወቃል።
አፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ በሞቃዲሾ የተፈጸመውንና ለበርካታ ንጹሃን ሞት፣ ለትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ውድመት ምክንያት የሆነውን የሽብር ጥቃት ማውገዛቸው ይታወሳል።