የሄዝቦላ ወታደራዊ አዛዥ እና የሀማስ የፖለቲካ መሪ መገደላቸውን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሯል
እስራኤል በደቡብ ሊቢኖስ በፈጸመችው ጥቃት በርካቶች ተገደሉ።
እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በምትገኘው ነቢያት ከተማ በመኖሪያ ህንጻ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 10 ሰዎች መገደላቸውን እና ሁለት ህጻናትን ጨምሮ አምስት ሰዎች መቁሰላቸውን ሮይተርስ የሀገሪቱን ዜና አገልግሎት ኤንኤንኤን ጠቅሶ ዘግቧል።
በጥቃቱ ሰለባዎች ሁሉም ሶሪያውያን መሆናቸውን የጠቀሰው ዘገባው፣በጥቃቱ የደረሰው አጠቃላይ ጥቃት ከዲኤንኤ ምርመራ በኋላ ይፋ ይደርጋ ብሏል።
የእስራኤል ጦር በጥቃቱ የሄዝቦላን የጦር መሳሪያ ማከማቻ ኢላማ ማድረጉን ገልጿል።እስራኤል ይህን ጥቃት የፈጸመችው በእስራኤል እና በሀማስ መካከል በዶሃ እየተካሄደ የነበረው የተኩስ አቁም ንግግር በትናንትናው እለት ከቆመ እና ተደራዳሪዎቹ በሚቀጥለው ሳምንት ለመገናኘት እቅድ በያዙት ወቅት ነው።
ሄዝቦላ ቆየት ብሎ ባወጣው መግለጫ እስራኤል በነቢያት ከተማ ላይ ለፈጸመችው ጥቃት በሰሜን እስራኤል የምትገኘውን አይለት ሀሽሀር ኪብቱዝ በመምታት የበቀል እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
ከሊባኖስ በተተኮሰ ሮኬት ሁለት የእስራኤል ወታደሮች መቁሰላቸውን የገለጸው የእስራኤል ጦር በአጠቃላይ 55 ሮኬቶች ከሊባኖስ ተተኩሰዋል ብሏል። ባለፈው እሁድ እለት የእስራኤል ድሮን በደቡባዊ ሊባኖስ በተሞተርሳይክል ላይ ባደረሰው ጥቃት አንድ ሰው ቆስሏል።
ባለፉት ሳምንታት በእስራኤል እና በሄዝቦላ መካከል ያለው ውጥረት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው፣ ሄዝቦላ አድርሶታል በተባለው ጥቃት በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለችው ጎላን ሀይት 12 ህጻናት እና ታዳጊዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
እስራኤል ለዚህ ግድያ ምላሽ የሰጠችው በቤሩስ ከተማ ዳርቻ የሄዝቦላን ወታደራዊ አዛዥ በመግደል ነበር።
የሄዝቦላ ወታደራዊ አዛዥ በቤሩት ከተማ ዳርቻ እና የሀማስ የፖለቲካ መሪ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን መገደሉን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሯል። ኢራን ለሀኒየህ ግድያ እስራኤልን እንደምትበቀል በተደጋጋሚ ዝታለች።