ኢትዮጵያ በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎቿ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልእክት አስተላለፈች
በሊባኖስና በቀጠናው የፀጥታ ስጋትና ውጥረት እየከፋ መምጣቱን የኢትዮጵያ ቆንስላ አስታውቋል
አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት ዜጎቻቸው ጥንቃቄ እንዲያደርና ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ አዘዋል
በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በቤሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ የቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ምልእክት አስተላለፈ።
እስራኤል የሃመስ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ እና የሊባሱ ሄዝቦላህ የጦር መሪ ፉአድ ችኩርን መግደሏን ተከትሎ፤ ኢራን በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።
የኢራንን ዛቻ ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ከፍተኛ ስጋት መንገሱም ተነግሯል።
የኢትዮጵያ የቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤ በሊባኖስ እና በቀጠናው ያለው ወቅታዊ የፀጥታ ስጋት እና ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱን አስታውቋል።
ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱ በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ደህንነት ለማስጠበቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በትኩረት እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።
በዚህም መሰረት በሊባኖስ የሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ኢትዮጵያውያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ማንኛውንም የተለየ ሁኔታ ሲገጥማቸው በቆንስላው የቀጥታ መስመር ስልክና ዋትሳአፕ እንዲያሳውቁ ጥሪ አስተላፏል።
እንዲሁም ከሊባኖስ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሰጡ መመሪያዎችን ወይም ምክሮችን ማከበር ይገባል ያለው ጽህፈት ቤቱ፤ በማንኛውም ሰልፎች ወይም ህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ከማድረግ እንዲቆጠቡም አሳስቧል።
በሊባኖስ እና አካባቢው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከታማኝ የዜና ምንጮች እና አፊሴላዊ ቻናሎች የሚወጡ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ክንውኖችን እንዲከታሉም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።
በሊባኖስና በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የፀጥታ ስጋት ሁኔታ እየተባሰ መምጣቱን ተከትሎ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት ዜጎቻቸው ጥንቃቄ እንዲያደርና ሊባስኖስን ለቀው እንዲወጡማዘዛቸው ይታወሳል።
በቤሩት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ፤ የአሜሪካ ዜጎች በተገኘው በማንኛውም የበረራ ቲኬት በአስቸኳይ ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ ያሳሰበ ሲሆን፤ ለቀው ለማይወጡ ደግሞ ለረጅም ጊዜ እቅድ እንዲያዘጋጁ እና መጠለያ ምሽግ ቦታ እንዲሆኑ አሳስቧል።
ፈረንሳይ፣ ብሪታኒያ እንዲሁም ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የንግድ በረራዎች ከመቋረጣቸው በፊት ሊባስን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ መሳሰባቸውም ይታወሳል።
ከሰሞኑ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የጦርነት ስጋት እየተባሰ መምጣቱን ተከትሎ ግዙፍ የዓለማች አየር መንገዶች ወደ እስራኤል፣ ሊባኖስ እና ኢራን የሚያደርጉትን በረራ አቁመዋል።