ሊባኖስን “ወደ ድንጋይ ዘመን እንመልሳታለን” - የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር
የመንግስታቱ ድርጅት በበኩሉ በሊባኖስ የሚጀመር ጦርነት አድማሱን ወደ ሶሪያና ሌሎች ሀገራት ያሰፋል ሲል አስጠንቅቋል
ሄዝቦላህ ባለፈው ሳምንት እስራኤል የድሮንና ሮኬት ጥቃታችን መቋቋም አትችልም ማለቱ ይታወሳል
እስራኤል ጎረቤቷን ሊባኖስ “ወደ ድንጋይ ዘመን” ልትመልሳት እንደምትችል አስጠነቀቀች።
በአሜሪካ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት፥ እስራኤል ከሊባኖስ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ ተናግረዋል።
“ጦርነቱን አንፈልገውም፤ ይሁን እንጂ በማንኛውም መንገድ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነን፤ ሄዝቦላህም ጦርነቱ ቢጀመር በሊባኖስ ላይ የሚደርሰውን ከባድ ኪሳራ ጠንቅቆ ያውቀዋል” ነው ያሉት።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት በበኩላቸው ከሄዝቦላህ ጋር የሚደረግ ጦርነት በመካከለኛው ምስራቅ ከባድ ቀውስ እንደሚያስከትል ነው ለጋላንት የነገሯቸው።
በጋዛው ጦርነት የእስራኤል ሁነኛ አጋር መሆኗን ያሳየችው አሜሪካ የሊባኖስ እና እስራኤል ውጥረት በዲፕሎማሲያዊ ንግግር እንዲፈታ ጥሪ ማቅረቧንም ፍራንስ 24 አስነብቧል።
ጀርመን እና ካናዳ በሊባኖስ የሚኖሩ ዜጎቻቸውን ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የመከሩ ሲሆን፥ ውጥረቱን የሚያረግብ ንግግር እንዲጀመር ጠይቀዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፍትስ ከጄኔቫ በሰጡት መግለጫ ሊባኖስ ላይ የሚጀመር ጦርነት ወደ ሶሪያና ሌሎች ሀገራት ሊስፋፋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የሊባኖስ ብሄራዊ የዜና ወኪል እስራኤል በትናንትናው እለት ብቻ 10 የአየር ጥቃቶችን መፈጸሟን ዘግቧል።
ሄዝቦላህ በአንጻሩ በእስራኤል የድንበር ከተሞች በሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ በ24 ስአት ውስጥ ስድስት ጥቃቶችን መፈጸሙን ነው ያስታወቀው።
የቡድኑ መሪ ሀሰን ናስራላህ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ እስራኤል በሊባኖስ ላይ ጦርነት ብታውጅ የሚደርስባትን ታውቀዋለች ሲሉ መዛታቸው ይታወሳል።
ናስራላህ “ጠላቶቻችን (እስራኤል) ለከባድ ጊዜ በሚመጥን ደረጃ ያደረግነውን ዝግጅት ያውቁታል፤ የድሮን እና ሮኬት ጥቃታችን ሊቋቋሙት አይችሉም” ነበር ያሉት።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንይሁ በጋዛ “መጠነ ሰፊው ዘመቻ” እየቀነሰ መሄዱን ካሳወቁ በኋላ 10ኛ ወሩን ሊይዝ የተቃረበው ጦርነት መቀዛቀዙ እየተነገረ ነው።
እስራኤል ከጋዛ የምታስወጣቸውን ወታደሮቿን ወደ ሊባኖስ ድንበር እንደምታሰማራ ኔታንያሁ መናገራቸውም ይታወሳል።