እስራኤል በሊባኖስ ላይ ጦርነት ከከፈተች የመጥፋት አደጋ እንደሚጋረጥባት ኢራን አስጠነቀቀች
እስራኤል በሊባኖሱ ሂዝቦላህ ላይ ይፋዊ ጦርነት ለማወጅ ዝግጅት ላይ መሆኗን ማስታወቋ ይታወሳል
ከዘጠን ወር በፊት የተጀመረው የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት አሁንም መቋጫ አላገኘም
እስራኤል በሊባኖስ ላይ ጦርነት ከከፈተች የመጥፋት አደጋ እንደሚጋረጥባት ኢራን አስጠነቀቀች፡፡
ለፍልስጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ በእስራኤል ላይ ያልታሰበ ጥቃት ከሰነዘረበት ዕለት አንስቶ በመካከለኛው ምስራቅ አለመረጋጋት እንደቀጠለ ነው፡፡
10 ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት በቀሩት በዚህ ጦርነት ከ37 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ሲገደሉ ከ1 ሺህ 200 በላይ እስራኤላዊያንም ተገድለዋል፡፡
በኢራን ይደገፋል የሚባለው የሊባኖሱ ሂዝቦላህ በጦርነቱ ላይ በቀጥታ ተሳትፎ እያደረገ ሲሆን ለሐማስ የቀጥታ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በእስራኤል ላይ የአየር ጥቃቶችን ሲያደርስ ቆይቷል፡፡
እስራኤል ከሰሞኑ እንዳሳወቀችው ከሆነ በጋዛ ስታደርገው የነበረውን ዘመቻ በመቀነስ ወደ ሊቦኖስ በማዞር ይፋዊ የአየር እና ምድር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዝግጅት እያደረገች መሆኗን አስታውቃለች፡፡
ይህንን ተከትሎ በርካታ የምዕራባዊን ሀገራት በሊባኖስ ያሉ ዜጎቻቸውን በማስወጣት ላይም ናቸው፡፡
የሂዝቦላህ ደጋፊ እንደሆነች የምትገለጸው ኢራን እስራኤልን አስጠንቅቃለች፡፡ በኒዮርክ ያለው የኢራን ኢምባሲ በኤክስ አካውንቱ እንዳስታወቀው እስራኤል ሊባኖስን ካጠቃች ደብዛዋ ሊጠፋ ይችላል ብሏል፡፡
ለእስራኤል የሀገርነት እውቅና የነፈገችው ኢራን እስራኤል በሊባኖስ ላይ ጦርነት ካወጀች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች ሁሉ የተቀናጀ ጥቃት እንደሚከፍቱም አስጠንቅቃለች፡፡
ይሁንና ኢራን በቀጥታ ወደ ጦርነቱ እንደምትገባ እና እንደማትገባ በይፋ ያልተናገረች ሲሆን በሊባኖስ ላይ ሙሉ ጦርነት ከታወጀ ግን እስራኤል ህልውናዋ የሚጠፋት ይሆናል ብሏል፡፡
ቱርክ ከሰሞኑ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣችው መግለጫ እስራኤል በሊባኖስ ላይ ይፋዊ ጦርነት ካወጀች ለሊባኖስ የቀጥታ ድጋፍ እንደምታደርግ አስጠንቅቃለች፡፡