በሜታ ኩባንያ ስር ያሉ መተግበሪያዎችም ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ጊዜ በመጫን አሁንም ተጽዕኗቸው ጉልህ መሆኑን አሳይተዋል
ሊጠናቀቅ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀረው 2023 በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ልማት ከፍተኛ እምርታ የታየበት አመት ነው።
የኦፕንኤአይ ንብረት የሆነው ቻትጂፒቲን ጨምሮ የጎግሉ ባርድ እና የማይክሮሶፍቱ ኮ ፓይለት መተግበሪያዎች በስፋት አገልግሎት ላይ ውለዋል።
እነዚህ መተግበሪያዎች በ2024ም የቢሊየኖች ምርጫ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
በ2023 ከጎግል ፕሌይ አልያም አፕ ስቶር ላይ በርካታ ሰዎች ያወረዷቸው መተግበሪያዎች ግን የቀደሙት ታዋቂ የማህበራዊ ትስስር ገጽ መተግበሪያዎች ናቸው።
በዚህ አመት አጠቃላይ ተጠቃሚዎቹ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን የደረሱለት ቲክቶክ በ2023 የመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ 672 ሚሊየን ሰዎች አውርደውታል።
የሜታ ንብረት የሆኑት ኢንስታግራም፣ ፌስቡክ እና ዋትስአፕም በድምሩ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ሰዎች የጫኗቸው መተግበሪያዎች በመሆን አሁንም አለማቀፍ ተቀባይነታቸው ጉልህ መሆኑን አሳይተዋል።
ስታቲስታ በ2023 በብዛት የተጫኑ ናቸው ብሎ ያወጣቸው 10 መተግበሪያዎች ቀጥሎ ቀርበዋል፦
1. ቲክቶክ - 672 ሚሊየን
2. ኢንስታግራም - 548 ሚሊየን
3. ፌስቡክ - 449 ሚሊየን
4. ዋትስአፕ - 424 ሚሊየን
5. ካፕከት - 357 ሚሊየን
6. ስናፕቻት - 330 ሚሊየን
7. ቴሌግራም - 310 ሚሊየን
8. ሰብወይ - 304 ሚሊየን
9. ሲምፕል ጋይስ - 254 ሚሊየን
10. ስፖቲፋይ - 238 ሚሊየን
እንደ ሜታ (የቀድሞው ፌስቡክ)፣ አፕል፣ አልፋቤት (ጎግል)፣ አማዞን እና ሌሎች ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ የጀመሯቸው ስራዎች የመተግበሪያዎቻቸውን ተፈላጊነት እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።