አሳሳቢው የስማርት ስልክ ሱሰኝነት ለምን ሴቶችን ይበልጥ ተጋላጭ አደረገ?
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት ከአለማችን ወጣቶች ሲሶው ለስማርት ስልክ ሱስ መጋለጡን አመላክቷል
ፊሊፒንስ እና ማሌዥያ በርካታ የስማርት ስልክ ሱሰኛ ያለባቸው ሀገራት ናቸው ተብሏል
በአለማችን ከ6 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ ሰዎች የስማርት ስልኮችን እንደሚጠቀሙ ይገመታል።
የስማርት ስልክ ተጠቃሚው ቁጥር ከሰባት አመት በፊት ከነበረበት በእጥፍ መጨመሩንም የስታስቲካ መረጃ ያሳያል።
ከስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር እኩል ከስልካቸው መነጠል የማይፈልጉ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሄዱ ተደጋግሞ ተጠቅሷል።
ባለፈው ሳምንት በአለማቀፉ የአዕምሮ ጤና ጆርናል ላይ የታተመ ጥናትም ከአለማችን ወጣት ስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ውስጥ ሲሶው አጠቃቀሙ ከመደበኛው በብዙ ርቀት አልፎ ሱስ ከመሆን ደርሷል ይላል።
ኦክስፎርድ እና ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ያደረጉት ጥናት የስማርት ስልክ ሱሰኝነት መላው አለምን እየፈተነ ያለ ጉዳይ መሆኑንና የአዕምሮ ጤና ጉዳቱም ከፍተኛ መሆኑንም ነው የጠቆመው።
እንቅልፍ ማዛባት፣ ፍርሃት፣ ድብርት እና ሌሎች ተያያዥ የአዕምሮ ጤናን የሚያዛቡ ችግሮች ከስማርት ስልኮች ሱሰኝነት ጋር በተገናኘ እየተበራከቱ ነውም ብሏል።
በ200 ሀገራት ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችን በማነጋገር የተሰራው የዳሰሳ ጥናት ከ19 እስከ 40 አመት ያሉ ወጣት ሴቶች ለስማርት ስልክ ሱስ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን አመላክቷል።
ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ስልካቸውን መልዕክት መላላክን ጨምሮ ማህበራዊ መስተጋብርን ለሚያሳድጉ ተግባራት ማዋላቸው ረጅም ስአት ስልክ እንዲጠቀሙ ሊያደርጋቸው እንደሚችል በመጥቀስ።
ከዚህም ባሻገር ከወንዶች በበለጠ ለድብርት እና ፍርሃት የሚጋለጡት ሴቶች ስማርት ስልኮቻቸውን ችግራቸውን መርሻ እያደረጉት ሊሆን እንደሚችልና ዝርዝር ጥናት ግን እንደሚያስፈልገው ነው የተጠቀሰው።
ጥናቱ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ለስማርት ስልክ ሱሰ ተጋላጭነታቸው ከፍ ብሎ መታየቱን አመላክቷል።
እንደ ፊሊፒንስ እና ማሌዥያ ያሉ ሀገራት ዜጎቻቸው ከስልካቸው መለያየትን የማይሹባቸው ተብለው በቀዳሚነት ተጠቅሰዋል፤ ጥናቱ አሜሪካን ከዚህ ዝርዝር ውስጥ ባያካትትም ሚሊየኖች ለስማርት ስልክ ሱስ መጋለጣቸውን የዴይሊ ሜል ዘገባ ያሳያል።
የስማርት ስልክ ሱሰኛ መሆናችን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ሊንኩን ተጭነው ያንብቡ