የዋትስአፕና ፌስቡክ መልዕክቶችን የሚሰርቀው መተግበሪያ
“ባሃሙት” የተባለ የህንዱ የመረጃ መንታፊ ቡድን የሰራው መተግበሪያ የአንድሮይድ ስልኮችን በስፋት እያጠቃ ነው ተብሏል
መተግበሪያው የድምጽና ጽሁፍ መልዕክቶችን፣ የስልክ ቁጥርና ሌሎች ሚስጢራዊ መረጃዎችን ይመነትፋል
የአንድሮይድ ስልክ ተጠቃሚዎች የዋትስአፕ እና ፌስቡክ መልዕክቶችን ከሚሰርቀው መተግብሪያ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ተመክሯል።
የሳይበር ጥናት ተቋምይ ሳይፊርማ እንዳስታወቀው አዲሱ የአንድሮይድ ስልኮችን በተለየ እያጠቃ ያለው መተግበሪያ “ሴፍቻት” ይሰኛል።
“ሴፍቻት” እንደ ሌሎች መተግበሪያዎች ሁሉ የተለያዩ መረጃዎችን ለመውሰድ ፈቃዳችን ይጠይቅና ምንተፋውን ይጀምራል።
ይህ መተግበሪያ በአሁኑ ወቅት ከፕሌይ ስቶር ቢወገድም በጫኑት ሰዎች ላይ የጥፋት ተልዕኮውን ቀጥሏል ይላል ሳይፍሪማ።
የዋትስአፕ እና ፌስቡክ መልዕልክት ልውውጣችን፣ የስልክ ቁጥሮች፣ የስልክ ንግግር ቅጂ እና የጽሁፍ መልዕክቶችን እየመነተፈም መተግበሪያውን ለስለላ አላማ ለገዙት ኩባንያዎች ያቀብላል።
“ሴፍቻት” የስልክ እና ኮምፒውተር መለያ ቁጥር (አይፒ አድራሻዎች)፣ የተጫኑ መተግበሪያዎች ዝርዝር፣ የስማርት ስልኩን ሙሉ መረጃ እና ሌሎች ሚስጢራዊ መረጃዎችንም ይሰርቃል ነው የተባለው።
የሳይፍሪማ ተመራማሪዎች ሰዎች መተግበሪያውን እንዲጭኑ የሚያስተዋውቀው እንዴት ነው የሚለውን አልጠቆሙም።
ይሁን እንጂ ምናልባትም ከተለያዩ ሀገራት መንግስታት ጋር በቅርበት ሊሰራ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
የህንዱ “ባሃሙት” የተባለ የመረጃ መንታፊ ቡድን ኩባንያ ይህን መተግበሪያ መረጃን ከሚመነትፍ ቫይረስ ጋር ለተጠቃሚዎች እንዳቀረበው የሳይፍሪማ መረጃ ያሳያል።
መተግበሪያው ከ2017 ጀምሮም የበርካታ የአንድሮይድ ስልኮች ተጠቃሚዎችን መረጃ ሲመነትፍ መቆየቱን ነው የሚገልጸው።
ባለፈው አመትም የአንድሮይድ ስልኮችን የሚሰልሉ ሀሰተኛ የቪፒኤን መተግበሪያዎችን ይሄው “ባሃሙት” የተባለው የመረጃ መንታፊ ቡድን ማሰራጨቱን ዴይሊ ሜል አስታውሷል።