ፑቲን ያቀረቡትን የክተት ጥሪ ተከትሎ በአንድ ቀን ብቻ 10 ሺህ ሩሲያውያን ለመዝመት ፈቃደኛ ሆኑ
የክተት ጥሪውን ተከትሎ በርካታ ሩሲያውያን ለወታደራዊ ጥሪው ምላሽ ሲሰጡ የሚያሳዩ ምስሎች እየወጡ ነው
ሩሲያ 300 ሺህ ለሚሆኑ ተጠባባቂ የጦር አባላት ጥሪ ማቅረቧ ይታወሳል
ፑቲን ያቀረቡትን የክተት ጥሪ ተከትሎ በአንድ ቀን ብቻ 10 ሺህ ሩሲያውያን ለመዝመት ፈቃደኛ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
ወደ ዘማቾቹ የጥሪ ወረቀቶችን ሳይጠብቁ ወደ ዩክሬኑ ጦርነት ለሚደረገው ዘመቻ ለመመዝገብ መምጣታቸውንም የሩሲያ የዜና ኤጀንሲዎች የሩሲያ ኢታማዦር ሹም ጽ/ቤት ዋቢ በማድረግ በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡
የሩሲያ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ቭላድሚር ጺምሊያንስኪ "በከፊል በተደረገው የክተት ጥሪ በመጀመሪያው ቀን ወደ 10ሺህ የሚጠጉ ዜጎች መጥሪያ ሳይጠብቁ በራሳቸው ፈቃድ ወደ ቅጥር ቢሮ ደርሰዋል" ሲሉ ለሩሲያ ኢንተርፋክስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
በንቅናቄው ዙሪያ ከግለሰቦችና ከድርጅቶች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሩሲያ መካላከያ የጥሪ ማዕከል ማቋቋሙንም ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን የክተት ጥሪውን ካቀረቡ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ዜጎች ለወታደራዊ ጥሪ ምላሽ ሲሰጡ የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ በመዘዋወር ላይ መሆናቸውም እየተነገረ ነው፡፡
በተለይም በሳይቤሪያ ያኪቲያ ከተማ፣ ወንዶች ወደ አውቶቡስ ከመሳፈራቸው በፊት ፊታቸው ደብዝዞ የቤተሰብ አባላትን ሲያቅፉና ሲሰናበቱ የሚያሳዩ ምስሎች መለቀቃቸው ዘገባው ያመለክታል፡፡
ታዋቂው የቴሌግራም ቻናል ማሽ የንቅናቄው አካል ሆኖ በምስራቅ ካባሮቭስክ ክልል አውሮፕላን ለመሳፈር የሚጠባበቁ ሰዎችን ረጅም ሰልፍ የሚያሳዩ ምስሎችን አሰራጭቷል።
በደቡባዊ የቼቺኒያ ሪፐብሊክ የተቀረጸ ነው የተባለ ሌላው ቪዲዮ ደግሞ በአካባቢው በሚገኝ ቅጥር ግቢ ውስጥ በፖሊሶች ታጅቦ በደርዘን የሚቆጠሩ ወጣቶችን የሚያሳይ መሆኑም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ሩሲያ 300 ሺህ ለሚሆኑ ተጠባባቂ የጦር አባላት ጥሪ ማቅረቧ አይዘነጋም፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እሮብ እለት ለሀገሪቱ ዜጎች ባደረጉት ንግግር "ሩሲያ የደህንነት ስጋት ከገባት ማንኛውንም መንገድ ትጠቀማለች፣ ይህ ቀልድ አይደለም" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዱማ በተሰኘው የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ዘመቻ አላማው እንዳልተቀየረ፣ በአራት የዩክሬን ግዛቶች ማለትም በሉሀንስክ፣ ዶንቴስክ፣ ካርኪቭ እና ዛፖራዚየ ግዛቶች ከቀጣዩ አርብ ጀምሮ ወደ ሩሲያ መቀላቀል የሚያስችላቸውን ህዝበ ውሳኔ ያካሂዳሉ ብለዋል።
በዚህም መሰረት ሩሲያ በዩክሬን ለጀመረችው ልዩ ዘመቻ ከዚህ በፊት ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ሩሲያዊያን ተጠባባቂ ሀይሎች በዩክሬን የተጀመረውን ዘመቻ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል ሲል ራሺያን ቱዴይ ዘግቧል።
የምዕራባውያን አላማ የተዳከመች እና የተከፋፈለች ሩሲያን መፍጠር እንደሆነ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ሉሀንስክ ግዛት ሙሉ ለሙሉ እንዲሁም ዶንቴስክ ግዛት ደግሞ በከፊል ከዩክሬን ነጻ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚንስትሩ ሰርጊ ሼጉ በበኩላቸው 300 ሺህ የሩሲያ ተጠባባቂ ጦር ጥሪ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።
ይህም ሩሲያ ካላት ተጠባባቂ ጦር ጥሪ ያቀረበችው ለአንድ በመቶ ለሚሆነው ሀይሏ ነው ተብሏል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ምድር ምዕራባውያን ጋር እየተዋጋች እንደሆነ የተናገሩት ሚንስትሩ የ70 ሀገራት ወታደራዊ ተቋማት እና ከ200 በላይ የሲቪል ሳተላይቶች ለዩክሬን ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ሚንስትሩ አክለውም ከ150 ሺህ በላይ የዩክሬን ወታደሮች መግደላቸው እና ስድስት ሺህ ገደማ የሩሲያ ወታደሮች ደግሞ እንደተገደሉባቸውም ገልጸዋል።