ሩሲያ 300 ሺህ ለሚሆኑ ተጠባባቂ የጦር አባላት ጥሪ አቀረበች
ሩሲያ የደህንነት ስጋት ከገባት ማንኛውንም መንገድ እንደምትጠቀም ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናገሩ
ሩሲያ በዩክሬን ምድር ከ70 ወታደራዊ ተቋማት ጋር እየተዋጋች መሆኑን ገልጻለች
ሩሲያ 300 ሺህ ለሚሆኑ ተጠባባቂ የጦር አባላት ጥሪ አቀረበች።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለሀገሪቱ ዜጎች ባደረጉት ንግግር "ሩሲያ የደህንነት ስጋት ከገባት ማንኛውንም መንገድ ትጠቀማለች፣ ይህ ቀልድ አይደለም" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዱማ በተሰኘው የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ዘመቻ አላማው እንዳልተቀየረ፣ በአራት የዩክሬን ግዛቶች ማለትም በሉሀንስክ፣ ዶንቴስክ፣ ካርኪቭ እና ዛፖራዚየ ግዛቶች ከቀጣዩ አርብ ጀምሮ ወደ ሩሲያ መቀላቀል የሚያስችላቸውን ህዝበ ውሳኔ ያካሂዳሉ ብለዋል።
በዚህም መሰረት ሩሲያ በዩክሬን ለጀመረችው ልዩ ዘመቻ ከዚህ በፊት ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ሩሲያዊያን ተጠባባቂ ሀይሎች በዩክሬን የተጀመረውን ዘመቻ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል ሲል ራሺያን ቱዴይ ዘግቧል።
የምዕራባውያን አላማ የተዳከመች እና የተከፋፈለች ሩሲያን መፍጠር እንደሆነ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ሉሀንስክ ግዛት ሙሉ ለሙሉ እንዲሁም ዶንቴስክ ግዛት ደግሞ በከፊል ከዩክሬን ነጻ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚንስትሩ ሰርጊ ሼጉ በበኩላቸው 300 ሺህ የሩሲያ ተጠባባቂ ጦር ጥሪ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።
ይህም ሩሲያ ካላት ተጠባባቂ ጦር ጥሪ ያቀረበችው ለአንድ በመቶ ለሚሆነው ሀይሏ ነው ተብሏል።
ሩሲያ በዩክሬን ምድር ምዕራባውያን ጋር እየተዋጋች እንደሆነ የተናገሩት ሚንስትሩ የ70 ሀገራት ወታደራዊ ተቋማት እና ከ200 በላይ የሲቪል ሳተላይቶች ለዩክሬን ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ሚንስትሩ አክለውም ከ150 ሺህ በላይ የዩክሬን ወታደሮች መግደላቸው እና ስድስት ሺህ ገደማ የሩሲያ ወታደሮች ደግሞ እንደተገደሉባቸውም ገልጸዋል።