ሩሲያ የዶንባስ ግዛቶችን ለመከላከል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም እንምትችል አስጠነቀቀች
የሩሲያ የህዝበ ውሳኔ እቅድ በዩክሬንና አጋሮቿ ከፍተኛ ውግዘት በማስተናገድ ላይ ነው
ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፤ የዶንባስ ግዛቶች ወደ ሩሲያ ይቀላቀላሉ "ወደ ኋላ መመለስ የለም" ሲሉም ተደምጠዋል
ሞስኮ፤ በሩሲያ ኃየሎች ስር የሚገኙትን የዶንባስ ግዛቶችን ለመከላከል ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር ጦር ማሳሪያ ልትጠቀም እንምትችል አስጠነቀቀች፡፡
የቀድሞ የሩስያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ሩሲያ በቅርቡ ምርጫ ለማካሄድ ባቀደችባቸው የዶንባስ ግዛቶች ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም አደጋ ለመከላከል ፤ አስፈላጊ ነው የሚባለው የትኛውም የጦር መሳሪያ በጥቅም ላይ ታውላለች ማለታቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
“ስትራቴጂክ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ጨምሮ ሞስኮ ያላትን የትኛውም የጦር መሳሪያ እንጠቀማለን” ብለዋል ሜድቬዴቭ፡፡
አሁን ላይ የሩስያ የጸጥታው ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር በመሆን ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ያሉት ሜድቬዴቭ በተገንጣይ ግዛቶች የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ወቅት መካሄዱ አይቀሬ መሆኑም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፤ የዶንባስ (ዶኔትስክ እና ሉሃንስክ) ሪፐብሊኮች እና ሌሎች ግዛቶች ወደ ሩሲያ ይቀበላሉ "ወደ ኋላ መመለስ የለም" ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የክሬምሊን ባለስልጣናት፤ የሩሲያ ጦር የተቆጣጠራቸው የዩክሬን ግዛቶች በተለይም በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙት አካባቢዎችን ወደ ሩሲያ ለመቀላቀል ህዝበ ውሳኔ ሊያካሂዱ መሆኑ ከሁለት ወራት በፊት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
የዩክሬን ግዛቶች የሆኑት ሉሃንስክ እና ዶኔትስክ ሪፐብሊኮች በሩሲያ፣ ሶሪያ እና ሰሜን ኮሪያ የሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና ማግኘታቸውም አይዘነጋም።
ያም ሆኖ ዩክሬን እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ድርጊቱን ኮንነዋል።
የሩሲው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬናውያን የሩሲያን ዜግነት ሊያገኙ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚያቀል አዲስ አዋጅ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
እርምጃውን የተቃወሙ የኪቭ ባለስልጣናት አዋጁ ህጋዊነት እንደሌለውና ተቀባይነት እንደማያገኝ ሲገልጹ መቆየታቸውም ይታወቃል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም የዩክሬን አጋሮች የሆኑት አሜሪካ፣ ጀርመንና ፈረንሳይም የክሬምሊን ባለስልጣናትን ህዝበ ውሳኔ የማካሄድ እቅድ አውግዘውታል፡፡
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ምርጫውን “የይስሙላ ድምጽ” ሲሉ፤ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ደግሞ “አሳፋሪ” ነው ሲሉ ገልጸውታል።
አሜሪካ በበኩሏ ሊካሄድ የታሰባ ምርጫ "የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መርሆዎችን የሚጥስ ነው" ብላለች፡፡
ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን ወደ ራሷ ለመቀላቀልን የምታደርገው ጥረት ፈጽሞ እንደማትቀበለም ጭምር ገልጻለች ዋሽንግተን፡፡