የ10 አመት ተኩስ አቁምና ትጥቅ መፍታት፤ የአሜሪካና ሃማስ ሚስጢራዊ ንግግር አንኳር ጉዳዮች
የፕሬዝዳንት ትራምፕ የታጋቾች ጉዳይ መልዕክተኛ አዳም ቦህለር በሚስጢራዊው ውይይት ሃማስ ያነሳቸውን ነጥቦች ይፋ አድርገዋል

መልዕክተኛው ከሃማስ መሪዎች ጋር ተስፋ ሰጪ ውይይት መደረጉንና በሳምንታት ውስጥ ስምምነት እንደሚደረስ እንደሚጠብቁም ተናግረዋል
አሜሪካ በሽብርተኝነት ከፈረጀችው ሃማስ መሪዎች ጋር በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ተገናኝታ መክራለች።
ውይይቱ በጋዛ የሚገኙ አሜሪካውያን ታጋቾች በማስለቀቅ ዙሪያ እንዳተኮረ ሲገለጽ ቢቆይም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በታጋቾች ጉዳይ የሚደረጉ ድርድሮችን እንዲመሩ ልዩ መልዕክተኛ አድርገው የሾሟቸው አዳም ቦህለር ዝርዝር ጉዳዮችን አንስተዋል።
መልዕክተኛው ከእስራኤሉ ቴሌቪዥን ካን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ሃማስ ከአምስት እስከ 10 አመት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ሁሉንም ታጋቾች እንደሚለቅና ትጥቅ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል" ብለዋል።
በሚስጢራዊው ውይይት የፍልስጤሙ ቡድን መሪዎች በጋዛ ውስጥ የሚገኙ የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ ዋሻዎችን ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት እና በሰርጡ ውስጥ ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ላለማድረግ ሃሳብ ማቅረባቸውንም ነው ያነሱት።
"የተወሰኑት ሃማስ የሚያነሳቸው ጉዳዮች በአንጻራዊነት ምክንያታዊና ሊሰራባቸው የሚችሉ ናቸው" ያሉት አዳም ቦህለር፥ ታጋቾችን ለማስለቀቅ "በሳምንታት ውስጥ ስምምነት ይደረሳል" ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
መልዕክተኛው ከእስራኤሉ ቻናል 14 ጋር ባደረጉት ቆይታ "ከሃማስ ጋር የሚደረስ የተኩስ አቁምም ሆነ ዘላቂ የሰላም ስምምነት የእስራኤልን ደህንነት ማረጋገጥ አለበት፤ ይህም ትጥቅ መፍታትንም ያካትታል፤ የሃማስ የፖለቲካ ተሳትፎ አክትሞለት ጋዛን መልሶ መገንባትም እንዲሁ" የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መመረጥ ብዙ ነገሮችን መለዋወጡን በመጥቀስም "ሰላም በጥንካሬ" እንደሚረጋገጥ ገልጸዋል።
የፍልስጤሙ ሃማስ ከአሜሪካ ጋር በቀጥታ ያደረገው ድርድር በኳታር መዲና ዶሃ መካሄዱን የቡድኑ መሪ የፖለቲካ አማካሪ ታሄር አል ኖኖ ለሬውተርስ አረጋግጠዋል።
የዶሃው ምክክር የአሜሪካ እና እስራኤል ጥምር ዜግነት ያላቸው ታጋቾችን በማስለቀቅ ላይ መተኮሩንም ነው ያነሱት።
በትራምፕ የታጋቾች ተደራዳሪ አዳም ቦህለር በኩል በቀረቡት የረጅም ጊዜ ተኩስ አቁም እና ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ ግን ማረጋገጫ አልሰጡም።
እስራኤልና ሃማስ የተቋረጠውን የጋዛ ተኩስ አቁም ለማስቀጠል ዛሬ በዶሃ ዳግም ድርድር እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
ሃማስ በጋዛ የሚገኙ ቀሪ 59 ታጋቾች (24ቱ በህይወት ያሉ) ለመልቀቅ በአሜሪካ አደራዳሪነት በሶስት ምዕራፍ እንዲተገበር ስምምነት የተደረሰበት ተኩስ አቁም ሁለተኛ ምዕራፍ መቀጠል አለበት እያለ ነው።
እስራኤል በበኩሉ ጦሯን ከጋዛ እንድታስወጣ በሚጠይቀው ሁለተኛ ምዕራፍ ተኩስ አቁም ላይ ድርድር ከመጀመር ይልቅ የ42 ቀናት የተኩስ አቁም ማራዘሚያ ምክረሃሳብ ማቅረቧ የሚታወስ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍም አዲስ የታጋቾችና እስረኞች ልውውጥ እና ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጫና ለማድረግ በነገው እለት ዶሃ እንደሚገቡ አክሲዮስ ዘግቧል።