እስራኤል በጋዛ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ አዘዘች
የእስራኤል የኢነርጂ ሚኒስትር ውሳኔውን ያሳለፉት ሃማስ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ተብሏል

እስራኤልና ሃማስ ከዘጠኝ ቀናት በፊት የተጠናቀቀውን ተኩስ አቁም ለማራዘም ዛሬ በዶሃ ድርድር ይጀምራሉ
እስራኤል በመላው ጋዛ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እንዲቋረጥ ማዘዟን አስታወቀች።
የሀገሪቱ የኢነርጂ ሚኒስትር ኢሊ ኮኸን "ታጋቾችን ለማስለቀቅ እና ሃማስ ከጦርነቱ በኋላ በጋዛ ህልውና እንዳይኖረው ለማረጋገጥ ሁሉንም አማራጮች እንጠቀማለን" ሲሉ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ የሰጡት ትዕዛዝ በተለይ የተጣራ የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ የሚውሉ ማሽኖችን ከስራ ውጭ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
የጠቅላይይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር በቀጣይም ወደ ጋዛ ውሃ እንዳይገባ ሊከለክል እንደሚችል ነው የተነገረው።
እስራኤል ባለፈው ሳምንት እሁድ ማንኛውም የሰብአዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ እንዳይገባ ማገዷ ይታወሳል።
በጥር ወር አጋማሽ ተፈጻሚ መሆን የጀመረው የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ እስራኤል ለ42 ቀናት ተኩስ አቁሙን ለማራዘም ሃሳብ አቅርባለች።
ሃማስ ግን በስምምነቱ መሰረት በሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ዙሪያ ለመደራደር እንጂ የተኩስ አቁም ማራዘሚያን እንደማይቀበል ማሳወቁን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ሃማስ ሁሉንም ታጋቾች መልቀቅ፤ እስራኤል ደግሞ ከጋዛ ወታደሮቿን ማስወጣት እንዳለባት በአሜሪካ አደራዳሪነት በተደረሰው የመጀመሪያ ስምምነት መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር።
እስራኤል ግን ተኩስ አቁሙን በማራዘም ቀሪ ስራ ይጠይቃል ያለችውን "ሃማስን የመደምሰስ" ዘመቻ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላት በተዘዋዋሪ እየገለጸች ነው።
በትናንትናው እለት ከግብጽ አደራዳሪዎች ጋር የመከረው የፍልስጤሙ ሃማስ አቋሙን እንዳለወጠ ያስታወቀ ሲሆን፥ በሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ላይ በፍጥነት ድርድር እንዲጀመር ጠይቋል።
ከመጀመሪያው ምዕራፍ በኋላ እንከን የገጠመውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማስቀጠል ዛሬ በኳታር መዲና ዶሃ ድርድር እንደሚጀመር ይጠበቃል።
እስራኤል ወደ ጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ መከልከሏ ከፍተኛ ተቃውሞ እያስነሳባት ነው።
"ለንጹሃን ህይወት መቀጠል ወሳኝ የሆኑ ሰብአዊ ድጋፎች እንዳይገቡ መከልከል የጅምላ ቅጣት" ነው ብሏል የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት።