የየመኑ ሃውቲ እስራኤል በጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳ አሳሰበ
ቴል አቪቭ እገዳውን በአራት ቀናት ውስጥ ካላነሳች በእስራኤል መርከቦች ላይ ጥቃት መክፈት እንደሚጀምር አስታውቋል

የፍልስጤሙ ሃማስ የሃውቲ ውሳኔ የ15 ወራቱ ያልተቋረጠ አጋርነት መቀጠሉን ያሳያል ብሏል
የየመኑ ሃውቲ እስራኤል በጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ የጣለችውን እገዳ በፍጥነት እንድታነሳ ጠየቀ።
የቡድኑ መሪ አብደል ማሊክ አል ሁቲ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት እስራኤል እገዳውን እንድታነሳ የአራት ቀናት ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል።
"ቀነ ገደቡ አደራዳሪዎች ጥረታቸውን (እገዳውን እንዲነሳ) እንዲቀጥሉ ለመፍቀድ ነው፤ ከአራት ቀናት በኋላ እገዳው ከቀጠለ፤ መድሃኒትና ምግብ ወደ ጋዛ እንዳይገባ ሁሉም መተላለፊያዎች ከተዘጉ ግን በጠላት እስራኤል ላይ የባህር ዘመቻችን እንጀምራለን" ብለዋል።
እስራኤል ከሃማስ ጋር የደረሰችው የ42 ቀናት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተኩስ አቁም ባለፈው ሳምንት ከተጠናቀቀ በኋላ ነው ማንኛውም ሰብአዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ እንዳይገባ ያገደችው።
ግብጽ እና ኳታር የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ ድርድር እንዲጀመር ጥረት ማድረጋቸውን ቢቀጥሉም የእርዳታ እገዳውን የሚያስነሳ ስምምነት አልተደረሰም።
እስራኤልና አጋሯ አሜሪካ ግን ሃማስ ሁሉንም ታጋቾች እንዲለቅ ከማስጠንቀቅ ውጪ ስለሰብአዊ ድጋፉ መቋረጥ ግድ የሰጣቸው አይመስሉም።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ሃማስ የተኩስ አቁሙን በ42 ቀናት ለማራዘም በአሜሪካ የቀረበውን ምክረሃሳብ ካልተቀበለ እስራኤል በጋዛ ዳግም ጦርነት ልትጀምር እንደምትችል ገልጿል።
ሃማስ ከ2 ሚሊየን በላይ የጋዛ ነዋሪዎች የከፋ ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ እንዳይገቡ አደራዳሪዎቹ ካይሮ እና ዶሃ በቴል አቪቭ ላይ ጫና እንዲያደርጉ መጠየቁን ሬውተስ ዘግቧል።
እስራኤል በጋዛ ጦርነት ካወጀች አንስቶ ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን ያሳየው የየመኑ ሃውቲ በትናንትናው እለት ያወጣውን መግለጫም አወድሷል።
በኢራን ድጋፍ ይደረግለታል የሚባለው ሃውቲ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፍልስጤማውያንን በሃይል ከጋዛ አስወጥቶ የመቆጣጠር እቅድን አጥብቆ እንደሚቃወም ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
ሃውቲዎች የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባሏቸው በቀይ ባህር በሚያልፉ መርከቦች ላይ ከ100 በላይ የሚሳኤልና ድሮን ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
ሁለት መርከቦችን አስምጠው በቀይ ባህር የሚጓዙ መርከበኞች አቅጣጫቸውን ወደ ረጅሙ የደቡብ አፍሪካ መስመር መለወጣቸውም አይዘነጋም።