ሃማስ፣ እስራኤልና አሜሪካ ግብጽ ስላቀረበችው የጋዛ መልሶ ግንባታ እቅድ ምን አሉ?
ግብፅ ያቀረበችውና 53 ቢሊየን ዶላር የሚያስፈልገው የጋዛ መልሶ ግንባታ እቅድ በአረብ ሀገራት መሪዎች ፀድቋል

በመልሶ ግንባታው ፍሊስጤማውያንን ሳያፈናቅል የሚካሄድ ሲሆን፤ ጋዛን ገለልተኛ ኮሚቴ እንዲያስተዳድር የሚያደርግ ነው ተብሏል
ግብጽ ያዘጋጀችው የጋዛ መልሶ ግንባታ እቅድ በአረብ ሀገራት ከጸደቀ በኋላ የተለያዩ የዓለም ሀገራት በእቅዱ ላይ አስተያየት እየሰጡ ይገኛሉ።
በካይሮ በትናንትናው እለት የተካሄደው የአረብ ሀገራት አስቸኳይ ጉባዔ ግብጽ ጋዛን መልሶ ለመገንባት ያቀረበችውን እቅድ ተቀብሎ አጸደቀ።
53 ቢሊየን ዶላር የሚያስፈልገው እቅዱ ጋዛን በ5 ዓመታት ውስጥ መልሶ መገንባት የሚያስችል ሲሆን፤ ፍሊስጤማውያንን ከመሬታቸው ሳያፈናቅል የሚካሄድ እና ጋዛን ገለልተኛ ኮሚቴ እንዲያስተዳድር የሚደርግ ነው ተብሏል።
ጋዛን የሚያስተዳድረው ሃማስ እቅዱ በአረብ ሀገራት ተቀባይነት አግኝቶ መጽደቁን ተከትሎ ጋዛን በፊሊስጤም አስተዳደር ስር መልሶ ለመገንባት በአረብ ሀገራት የተደረሰውን ውሳኔ በደስታ እንደሚቀበለው አስታውቋል።
እቅዱ ወደ መሬት ወርዶ እንዲተገበር የጠየቀው ሃማስ፤ የማክሰኘው የአረብ ሊግ ሀገራት ጉባዔን ለፍሊስጤማውያን ድጋፍ አንድ እርምጃ ነው ብሎታል።
"ጋዛን መልሶ የመገንባት እቅድ በደስታ እንቀበላለን” ያለው ሃማስ፤ ለስኬታማነቱ የሚያስፈልጉ ሁሉም ጥረቶች እንዲደረጉም ጥሪ አቅርቧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በበኩሉ ግብጽ ጋዛን መልሶ ለመገንባት ያስችላል በሚል ያቀረበችውን እቅድ ውድቅ አድርጓል።
እቅዱ "ጋዛ በአሁኑ ጊዜ ለመኖሪያነት አመቺ አለመሆኗን እንዲሁም ነዋሪዎቿ በፍርስራሾች እና ባልተፈነዱ ፈንጂዎች ውስጥ መኖር አይችሉም የሚለውን እውነታ አለተመለከተም" ብሏል።
እስራኤልም ግብጽ ጋዛን መልሶ ለመገንባት ያስችላል በሚል ያቀረበችውን እቅድ “መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ” ነው በሚል ውድቅ አድርጋለች።
የጋዛ መልሶ መገንታን እንዲመራ በእቅዱ የተገለፀው የፍሊስጤም አስተዳደር እና የተመድ የፍሊስጤም ስደተኞች ድርጅትን በሙስና እና ሽብርተኝነት በመርዳትም ከሳለች።
የግብጽ የጋዛ መልሶ ግንባታ እቅድ በውስጡ ምን ይዟል?
ከጋዛ መልሶ ግንባታ ጋር በተያያዘ ግብፅ ትራምፕ "የጋዛ ሪቪዬራ" እቅድ አማራጭ የሆነ እቅድ ይፋ ያደረገች ሲሆን፤ እቅዱ 53 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ እና አምስት አመታትን እንደሚወስድ ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ግብጽ ያዘጋጀችው እቅድ ፍልስጤማውያን "በመሬታቸው እንዲቆዩ" የሚያስችል ነው ብለዋል።
በእቅዱ መሰረት የመጀመሪያው ስድስት ወራት የማገገሚያ ምዕራፍ ሲሆን፤ በዚህም ፍርስራሾችን በማንሳት እና በ3 ቢሊዮን ዶላር ጊዜያዊ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት ላይ ያተኮረ መሆኑን አስታውቀዋል።
የመጀመሪያ ምዕራፍ በትክክል ከሄደ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ 200 ሺህ መኖሪያ ቤቶችን የጋዛ የመገንባት ሂደት ይከናዋነል ብለዋል።
በእቅዱ መሰረት በፈረንጆቹ በ2030 እቅዱ ለ3 ሚሊዮን ሰዎች ሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ቤቶች ግንባታ እንዲሁም የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የኢንዱስትሪ ዞኖች፣ ሆቴሎች እና መናፈሻ ፓርኮች ግንባታ እንደሚጠናቀቅም ተመላክቷል።
የአረብ ሀገራት አስቸኳይ ጉባዔ ላይ የቀረበው የጋዛ እቅድ ጋዛን የመካከለኛው ምስራቅ ሪቬራ አደርጋለሁ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን የሚፎካከር ነው።
ፕሬዝደንት ትራምፕ አሜሪካ ጋዛን በቁጥጥሯ ስር እንደምታደርግ፣ 2.2 ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎቿን ወደ ሌላ ሀገር እንደምታዛውርና "የመካከለኛው ምስራቅ ውብ ቦታ" እንደሚያደርጉ መናገራቸው የአረቡን አለም አበሳጭቷል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ የአረብ ሀገራት በተለይም ግብጽና ጆርዳን 16 ወራት በዘለቀው የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት የወደመችው ጋዛ እስከምትጸዳና መልሳ እስከምትገነባ በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያንን እንዲያስጠልሏቸው ጫና ሲያደርጉ ቆይተወዋል።
ነገርግን የአረብ ሀገራት ትራምፕ ያቀረቡትን ሀሳብ በጽኑ ተቃውመውታል።
የአረብ ሀገራት ፍልስጤማውያን ከቦታቸው ሳይፈናቀሉ የመልሶ ግንባታው አካል መሆን ይጠባቸዋል የሚለውን ሀሳብም ደግፈዋል።