በሱዳን በጎሳ ግጭት ምክንያት በአንድ ሳምንት 100 ሰዎች ተገደሉ
ግጭቱ በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ነው ተብሏል
በአካባቢው በተነሳው ግጭት 20 መንደሮች መቃጠላቸው ተሰምቷል
በሱዳን ዳርፉር ግዛት በተነሳ የጎሳ ግጭት ምክንያት ምክንያት 100 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡
የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ እና አንድ የጎሳ መሪ እንዳስታወቁት በአንድ ሳምንት ውስጥ በጎሳ ግጭት መነሻነት 100 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ግጭቱ የተነሳው በአረብ እና በአፍሪካ ጎሳዎች መካከል መሆኑን ዋሸንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስተባባሪ ቶቢ ሃርዋርድ ግጭቱ የተነሳው ኩለቡስ በምትባል የምስራቅ ዳርፉር ግዛት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ኮሚሽኑ አስተባባሪ መረጃ ከሆነ የአረብ እና የአፍሪካ ጎሳዎች ግጭቱን የጀመሩት በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ነው፡፡ የአካባቢው አረብ ሚሊሻዎች በአካባቢው ያሉ መንደሮችን ማጥቃታቸውና ሺዎች እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
አብካር አል ታወም የተባሉ የጎሳ መሪ ሚሊሻዎቹ 20 መንደሮች ያቃጠሉ ሲሆን በዚህም የ 62 ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል ተብሏል፡፡ በዚህ ግጭት የሞቱ ሌሎች ብዙ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ጥቃት አድራሾቹ የውኃ ሃብቶችን መቆጣጠራቸውንና የሰብዓዊ ሁኔታውን እንዲጋጋል ማድረጋቸውንም የጎሳ መሪው ገልጸዋል ሲል ዋሸንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ሌላ የጎሳ መሪ በበኩላቸው አንድ ሳምንት በነበረው ግጭት 5 ሺ ቤተሰቦች መፈናቀላቸው የተሰማ ሲሆን ባለስልጣናት ወደ አካባቢው ተጨማሪ ጦር እንዲሰማራ አድርገዋል፡፡