ግጭቱ በቻድ ድንበር አቅራቢያ ያጋጠመ ነው ተብሏል
በሱዳን ዳርፉር በተጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በትንሹ 19 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ፡፡
ግጭቱ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ በቻድ ድንበር አቅራቢያ በምዕራባዊ ዳርፉር ጀበል ሙን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ያጋጠመ ሲሆን 5 ሰዎችም ተጎድተዋል ተብሏል፡፡
ከአሁን ቀደምም በአካባቢው ተመሳሳይ ግጭቶች በተደጋጋሚ አጋጥመው የበርካቶችን ህይወት ቀጥፈዋል፡፡ አራት ያህል መንደሮች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውንም ነው የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ አካላት ያስታወቁት፡፡
ግጭቱ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የጃንጃዊድ ሚሊሻዎች ሳይፈጸም እንዳልቀረም አስተባባሪዎቹ ለኤ.ኤፍ.ፒ ተናግረዋል፡፡
ብዙዎቹ የጃንጃዊድ ሚሊሻዎች በሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳገሎ ወደሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መቀላቀላቸው ይነገራል፡፡
ዳርፉር በእርስበርስ ግጭቶች የሚታወቅ ነው፡፡ በፈረንጆቹ 2003 በተቀሰቀሰ የእር በእርስ ጦርነት በዳርፉት 300 ሺ ሰዎች መገደላቸውና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች መፈናቀላቸውን ተመድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡