የግጭቱ የተከሰተው “አረብ ነን” እና “ጥቁር ነን” በሚሉ ሁለት ጎሳዎች መካከል ነው
በሱዳኗ ዳርፉር ግዛት በተከሰተ ግጭት ከ167 በላይ ሱዳናዊያን ሲገደሉ 98 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል።
በምዕራብ ዳርፉር ካሪናክ በትሰኘት ከተማ በተከሰተው ግጭት የሟቾች ቁጥር ወደ 200 ሊያሻቅብ ይችላል የተባለ ሲሆን፤ በርካቶች ደግሞ ከባድ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው የስደተኞች እና ተፈናቃይ ኤጀንሲ ቢሮ ገልጿል።
ከሟቾቹ መካከልም ስድስቱ መምህራን ናቸው የተባለ ሲሆን፤ የግጭቱ መነሻ ባሳለፍነው አርብ “አረብ ነን” እና “ጥቁር ነን” በሚሉ ሁለት ጎሳዎች መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት በትናንትናው ዕለት ድጋሚ በማገርሸቱ ነው።
ይህ ጎሳን መሰረት ያደረገ ግጭት ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመስፋፋት ላይ ነው የተባለ ሲሆን፤ አልጀኒና ወደ ተሰኘው ሌላኛው የዳርፉር ከተማ ሰዎች በመጎዳት ላይ ናቸው ተብሏል።
በካሪናክ ከተማ የተከሰተውን ግጭት በመቃወምም በአጎራባች እና ሌሎች ከተሞች የሚኖሩ ሱዳናዊያን መንገዶችን በመዝጋት ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
በሱዳን ከሁለት ዓመት በፊት በዳርፉር በተከሰት የጎሳ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸው ያጡ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ወደ ጎረቤት አገር ቻድ መሰደዳቸው ይታወሳል።