በ2023 100 ዝነኛ አፍሪካዋያን ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ በነማን ተወከለች?
ረፑቴሽን ፖል ኢንተርናሽናል የተባለው አለም አቀፍ ተቋም ባወጣው ዝርዝር ውስጥ አራት ኢትዮጵያውያን ተጽዕኖ ፈጣሪ ተብለው ተካተዋል
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ዶክተር ሊያ ታደስ፣ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶክተር) እና ፍጹም አሰፋ (ዶክተር) ናቸው በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት
በአፍሪካ በአዲሱ የፈረንጆቹ አመት 2023 ዝናቸው ከፍ ብሎ ይታያል ተብለው የሚጠበቁ 100 ሰዎች ዝርዝር ይፋ ሆኗል።
ረፑቴሽን ፖል ኢንተርናሽናል የተባለው አለም አቀፍ ተቋም ባወጣው ዝርዝር ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ግንባር ቀደም ስራ የሰሩ አፍሪካውያን ተካተዋል።
በመንግስት እና ተቋማት መሪነት፣ በመዝናኛ፣ በሰብአዊ መብት ማስከበርና ማማከር፣ በትምህርት እና የቢዝነስ ዘርፎች የተመረጡት አፍሪካውያን ተጽዕኖ ፈታሪዎች በ2023 አርአያ የሚሆን ተግባር እንደሚከውኑ ይጠበቃል ብሏል ረፑቴሽን ፖል ኢንተርናሽናል።
ኢትዮጵያም በዚህ የ100 ተጽዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን ዝርዝር ውስጥ በአራት ሰዎች ተወክላለች።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአመራር ዘርፍ ከተመረጡት ውስጥ ተካተዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እና የፕላን እና ልማት ኮሚሽን ሃላፊ ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶክተር) ማህበራዊ ሃላፊነትን በመወጣትና ህይወትን በማቅለል በህዝብ ዘንድ ከበሬታ ካገኙ ምርጥ 100 አፍሪካውያን ውስጥ ስማቸው ስፍሯል።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ኢጋድ ዋና ጸሃፊው ወርቅነህ ገበየሁም (ዶክተር) በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት ኢትዮጵያውያን መካከል ይገኙበታል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የማላዊ አቻቸው ላዛረስ ቻክዌራ በመንግስት አስተዳደር እና ፖሊሲ ዘርፍ በመሪዎች ደረጃ የተከበረ ስራን እንደሚከውኑ ታምኖባቸው በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል።
በአፍሪካ አዲስ የስራ ፈጠራን ያስተዋወቁና ድጋፍ ያደረጉ ግለስቦችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም በዚሁ የእውቅና ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል ተብሏል።
የኬንያ የፍትህ ሚኒስትር ማርታ ኮሜ እና ናይጀሪያዊቷ አይሻ የሱፍ በሰብአዊ መብት ተሟጋችነት 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን ዝርዝር ተቀላቅለዋል።
በተለያዩ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ተቋማት ከፍተኛ አበርክቶ ያላቸው አፍሪካውያንም ረፑቴሽን ፖል ኢንተርናሽናል ባወጣው ዝርዝር መካተታቸው ታውቋል።
በጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የቢቢሲዋ ዘይነብ ባዳዊ ተመርጣለች።