ብሪታንያዊው ትንቢተኛ በ2023 በቻይና አቢዮት ይነሳል አለ
ክሬግ ፓርከር፥ የብሪታንያን ከአውሮፓ ህብረት፣ የትራምፕን ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥና የንግስት ኤልሳቤጥን ህልፈት አስቀድሞ ተንብዮ ተሳክቶለታል
2023 እና 2024 ለአለማችን ፈታኝ ዓመታት ናቸው ያለ ፓርከር፥ ቻይና ከታይዋን ጋር ጦርነት ውስጥ እንደምትገባም ነው የተናገረው
ፈረንሳዊው ኮከብ ቆጣሪ ኖስትራደመስ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተነበያቸው ነገሮች ከ400 አመታት በኋላም እውን እየሆኑ እየታየ ነው።
“የዘመኑ ኖስትራደመስ” ነው የተባለለት እንግሊዛዊ ክሬግ ሃሚልተን ፓርከርም ከዚህ ቀደም ይሆናሉ ያላቸው ተሳክተው ታይተዋል።
ፓርከው ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት እንደምትወጣ ከአመታት በፊት ትንቢቱን ተናግሯል።
ቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕም 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ ሲናገር ብዙዎች ቢጠራጠሩም ትራምፕ በነጩ ቤተመንግስት ከ2017 እስከ 2021 ቆይተዋል።
ፓርከር ንግስት ኤልሳቤጥ ዳግማዊ በ96 አመታቸው ህይወታቸው እንደሚያልፍም ከአመታት በፊት መናገሩን ነው ሜትሮ ያወሳው።
የንግስት ኤልሳቤጥን ህልፈት ተከትሎ የብሪታንያ ንጉስ የሆኑት የንግስቷ የበኩል ልጅጅ ቻርለስም በእንቁላል ሲመታ ታይቶኛል ባለ በሳምንታት ልዩነት ንጉሱ ክስተቱ ገጥሟቸዋል።
በ20ዎቹ እድሜ ላይ እያለ ወደ ህንድ ካደረገው ጉዞ በኋላ የመተንበይ ጥበብን ያዳበረው የ68 አመቱ ክሬግ ፓርከር፥ በ2023 እና 2024 አለማችን የሚገጥማትን ፈተናም በድረ ገጹ አጋርቷል።
“በያዝነው የፈረንጆቹ አመትም ሆነ በ2024 ሶስተኛው የአለም ጦርነት አይቀሰቀስም” ያለው ፓርከር፥ ነገር ግን ሃያላን ሀገራት አለማቀፋዊ ትብብርን እርግፍ አርገው ትተው የተናጠል ፉክክራቸውን ይገፉበታል ሲል ትንበያውን አስቀምጧ።
በ2023 ትልቁ አሳሳቢ ጉዳይ የምግብ እጥረት ነው፤ ይህ ችግር ምዕራባውያንንም የሚያጠቃ ሲሆን የሃይል አቅርቦት እጥረትም እንደ ብሪታንያ ባሉ ሀገራት አስቸኳይ ምርጫን ሊያስከትል ይችላል ብሏል ፓርከር።
በታይዋን የባህር ክልል ሁለት መርከቦች እንደሚጋጩ ያነሳው ክሬግ፥ ታይፒ ከቤጂንግ ጋር ወደለየለት ጦርነት እንደምትገባም ትንበያውን ያስቀምጣል።
እንደእርሱ ነገን የመመልከት ብቃት ያዳበረችው ባለቤቱ ጄንም በቻይና የሺንግ ስርወመንግስትን የሚጥል አቢዮት እንደሚነሳ መተንበዩዋን ተናግሯል።
የዩክሬኑ ጦርነትም መቀጠሉ አይቀሬ ቢሆንም ሶስተኛውን የአለም ጦርነት አያስከትልም የሚለውን ትንበያውን አክሏል።
ዴይሊ ሜል ላይ የወጣ ዘገባ ግን ፈረንሳዊው ኮከብ ቆጣሪ ኖስትራዳመስ በ1555 ለህትመት እንዳበቃው “ለ ፕሮፌሲስ” የተሰኘው መጽሃፍ አይነት የአለማችን መጻኢ የሚያሳይ የለም ይላል።
የአሜሪካውን የ9/11 ጥቃትን ጨምሮ የአዶልፍ ሂትለርን ስጋትነትና የአሁኑን ዘመን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ( አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) አስቀድሞ የተነበየው ኖስትራዳመስ፥ በ2023 ለሰባት ወራት የሚዘልቅ ከባድ ጦርነት እንደሚኖር ከ467 አመት በፊት ተንብዩዋል።
ይህም የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ነው ወይስ በታይዋን ጉዳይ ቻይና ከአሜሪካ ልትገባበት የምትችለው ጦርነት የሚለው ባለሙያዎችን ለሁለት ከፍሏል።