በያዝነው 2023 ዓመት የዓለማችን ኢኮኖሚ ብርቱ ፈተና እንደሚገጥመው ተገለጸ
የዩክሬን ጦርነት፣ የብድር ወለድ እና የኮሮና ቫይረስ ለዓለም ኢኮኖሚ መፈተን ዋነኛ ምክንያት ናቸው ተብሏል
እንደ ዓለም አቀፉ አይኤምኤፍ ማስጠንቀቂያ ከሆነ ሲሶው የዓለም ኢኮኖሚ ወደኋላ የመመለስ አደጋ ተጋርጦበታል
በያዝነው 2023 ዓመት የዓለማችን ኢኮኖሚ ብርቱ ፈተና እንደሚገጥመው ተገለጸ።
ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም አይኤምኤፍ ዓለማችን በአዲሱ የ2023 ዓመት ሊኖራት ስለሚችለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ሪፖርት አውጥቷል፡፡
የተቋሙ ዳይሬክተር ክርስታሊና ጆርጄቫ እንዳሉት በ2023 ዓመት ከዓለም ኢኮኖሚ ሲሶው ወደ ኋላ ይመለሳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
በተለይም የአሜሪካ፣ ቻይና እና አውሮፓ የኢኮኖሚ እድገታቸው ባለበት አልያም ወደኋላ ይመለሳል ያሉት ዳይሬክተሯ የዩክሬን ጦርነት፣ ኮሮና ቫይረስ፣ የወለድ ምጣኔ መጨመር እና የወጋ ግሽበት ለኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ዋኘኞቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡
- አይኤምኤፍ የዓለምን የኢኮኖሚ ድቀት ለማስቀረት “የተቀናጀ የፖሊሲ እርማጃ መውሰድ” አስፈላጊ ነው ሲል አሳሰበ
- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 7 ነጥብ 5 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ
ተቋሙ ባሳለፍነው 2022 ዓመት ዓለማችን ሊኖራት ስለሚችለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ትንበያውን አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ መናሩን ተከትሎ ትንበያውን አቁሞ ነበር፡፡
በተያዘው የፈረንጆቹ 2023 ዓመትም የዓለማችን ኢኮኖሚ በተለይም የኮሮና ቫይረስ በቻይና ማገርሸቱ የቤጂንግ እና በቻይና ላይ የተመሰረተው የእስያ ኢኮኖሚ ክፉኛ ሊጎዳ እንደሚችል ድርጅቱ ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
በዩክሬን ጦርነት እና በዋጋ ግሽበት ምክንያትም የአሜሪካ እና አውሮፓ ኢኮኖሚ እንደሚፈተን የገለጸው ይሄው ተቋም በተለይም ሸማቾች የመግዛት ፍላጎታቸው ስለሚቀንስ ኢኮኖሚው ወደኋላ ሊመለስ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
ታዳጊ ሀገራትም የበለጸጉ ሀገራት ኢኮኖሚ ስለሚጎዳ ብድር እንመልሱ ጫና ሊፈጥሩ ከመቻላቸው ባለፈ አምራች ኢንዱስትሪዎቻቸው በቂ ምርት አምርተው እንዳይልኩ ሊያደርግ ይችላልም ተብሏል፡፡
በተለይም ወደ አፍሪካ፣ አውሮፓ እና ሌሎች አህጉራት ምርቶችን በመላክ የሚታወቁት የቻይና ኢንዱስትሪዎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ምርት በማቆም ላይ መሆናቸው በዓለም ላይ የምርት እጥረት እና የዋጋ ግሽበት ሊያጋጥም እንደሚችል ተሰግቷል፡፡