በአሜሪካ ሎሳንጀለስ የተከሰተው ሰደድ አሳት ወደ ሆሊውድ ኮረብታዎች እየተስፋፋ መሆኑ ተገለጸ
ከ100 ሺ በላይ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል
አኩ ዌዘር የተባለው ተቋም በእሳት አደጋው የደረሰው የኢኮኖሚ ጉዳት ከ 50 ቢሊዮን በላይ እንደሚገመት ገልጿል
በአሜሪካ ሎሳንጀለስ ዙሪያ የተቀሰቀሰው ከባድ የሰደድ እሳት አደጋ ትናንት ምሽት ጀምሮ ወደ ሆሊውድ ኮረብታዎች እየተስፋፋ መሆኑ ተገልጿል።
ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በርካታ ቦታዎችን በፍጥነት ያዳረሰው በደረቅ ንፋስ እየተፋፋመ ያለው እሳት የማጥፋት ዘመቻውን ያከበደው ሲሆን ከ100 ሺ በላይ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል።
"የእሳት ማዕበሉ ትልቅ ነው" ሲሉ በጋና የነበራቸውን ጉብኝት አቋርጠው የተመለሱት የሎሳንጀለስ ከንቲባ ካሬን ባስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። አዲስ እሳት በሆሊውድ ኮረብታዎች ላይ ትናንት ምሸት መቀስቀሱን እና በርካቶች አካቢያዎቸን እንዲለቁ መደረጋቸውን የእሳት አደጋ ኃላፊው ክርስቲን ክሮውሊይ ገልጸዋል።
የከተማዋ ባለስጣናት እንደገለጹት በሎሳንጀለስ ስድስት ቦታዎች በእሳት የተያያዙ ሲሆን በከተማዋ ምስራቃዊ እና ምዕራባዊ ክንፎች በኩል ያሉትን ጨምሮ አራቱን መቆጣጠር አልተቻለም።
ትናንት ምሽት በሎሳንጀለስ ኮረብታዎች የተከተሰው "ሰንሴት ፋየር" 20 ሄክታር የሚሸፍን ቦታ አውድሟል። የአሳት አደጋ ሰራተኞች በሄሊክተር በመታገዝ የአሳቱን ነበልባል በማጥፋት እንዳይሳፋፋ ማድረግ ችለዋል።
የሎሳንጀለስ የአሳት አደጋ ክፍል በሆሊውድ አካባቢ ባሉ መንደሮች የሚኖሩ ነዋሪዎች እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
በሎሳንጀለስ ምዕራብ በኩል የተከሰተው የፓሊሳደስ እሳት 6406 ሄክታር እና በሳንታ ሞኒካ እና ማሊቡ ኮረብታዎች መካከል ማክሰኞ እለት ፓሲፊክ ውቅያኖስ እስከሚደርስ ድረስ በርካታ መሰረተ ልማቶችን ያወደመ ሲሆን በምስራቅ በኩል ደግሞ 4289 ሄክታር ቦታ ከማውደሙ በተጨማሪ አምስት ሰዎችን ገድሏል።
አኩ ዌዘር የተባለው የግል የትንበያ ተቋም በእሳት አደጋው የደረሰው የኢኮኖሚ ጉዳት ከ 50 ቢሊዮን በላይ እንደሚገመት ገልጿል።