የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናዊ ቅርጽ በተቀየረበት ወቅት ሊባኖስ ፕሬዝዳንቷን በፓርላማ ልትመርጥ ነው
ለሁለት አመታት ያለ ፕሬዝዳንት የቆየችው ሀገር ከጦርነት መልስ በነገው ዕለት በፓርላማ ፕሬዝዳንቷን ትመርጣለች
እስራኤል ካካሄደችው ጦርነት እና ከበሽር አላሳድ መውረድ ጋር በተያያዘ ቀጠናዊ ቅርጽ ለውጥ በታየበት ሁኔታ አዲስ የሚሾመው መሪ ሀገሪቱን በማረጋጋት ትልቅ ሀላፊነት ይጠብቀዋል
ላለፉት ወራት ከእስራኤል ጋር ሰፊ ጦርነት ስታካሄድ የሰነበተችው ሊባኖስ በነገው ዕለት በፓርላማ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ቀጠሮ መያዟ ተነግሯል፡፡
የሚሼል አውን የስልጣን ዘመን በጥቅምት 2022 ካበቃ በኋላ 128 መቀመጫዎች ባሉት ፓርላማ ውስጥ ከሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዳቸውም የራሳቸውን እጩ ለማስመረጥ የሚያስችል በቂ መቀመጫ ሳይኖራቸው ቆይተዋል፡፡
በዚህ የተነሳም እስካሁን ድረስ በጋራ ስምምነት ወይም በጥምር መንግስት እጩ አቅርበው መስማማት አልቻሉም።
በአሳድ ሲመራ የነበረው የሶሪያ መንግስት በቀጥታም ሆነ እንደ ሄዝቦላህ ባሉ አጋሮች አማካኝነት በሊባኖስ ፖለቲካ ውስጥ ለአስርት አመታት ተጽዕኖውን ሲያሳድር መቆየቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሄዝቦላህ እና በፓርላማ አፈጉባዔ ናቢህ በሪ የሚመራው የሺዓ አማል ንቅናቄ ላለፉት ሁለት አመታት እጩ አድርገው ያቀረቧቸው ሱሌይማን ፍራንጊህ ላይ ያላቸውን ድጋፍ በማንሳት ይበልጥ ተቀባይነት ይኖሯቸዋል ያሏቸውን ሶስት ከፍተኛ ባለስልጣን ዕጬ አድርጎ ለማቅረብ ማሰባቸው ተሰምቷል፡፡
በአሜሪካ ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸው የሚባሉት የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል ጆሴፍ አዎን ፣ በአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት እና የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር ጂሃድ አዙር እንዲሁም የሀገሪቱ ደህንነት ኤጂንሲ ሀላፊ ሜጀር ጄኔራል ኤልያስ አልባይሳሪ ሰፊ ትኩረትን ከላገኙ እጮዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል ጆሴፍ አዎን ከፍተኛ የማሸነፍ እድል የተሰጣቸው ሲሆን፤ ዕጩዎቹ ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመሾም በመጀመሪያው ዙር 86 ወይም በሁለተኛው ዙር 65 ድምጽ ሊያገኙ ይገባል፡፡
የምዕራባውያን እና ቀጠናዊ ፍላጎትን የሚያንፀባርቁ የፈረንሳይ እና የሳዑዲ ልዑካን በዛሬው እለት በቤሩት ከሊባኖስ ፖለቲከኞች ጋር ተገናኝተዋል።
ሳኡዲ በሊባኖስ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ ለመፍጠር ከኢራን እና ከሄዝቦላህ ጋር ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ እንደነበረች ይታወሳል፡፡
የሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሊባኖስን የፖለቲካ ተቋማት ለማጠናከር በአሜሪካን ወይም በሌሎች የውጭ ተዋንያን ጣልቃገብነት ሳይሆን ቀጣዩን ፕሬዚዳንት የመምረጥ ሀላፊነት የሊባኖሳውያን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ በቢሯቸው በኩል ባወጡት መግለጫ “ፈጣሪ ከፈቀደ ነገ አዲስ ፕሬዝዳንት ይኖረናል በዚህም ደስተና ነኝ” ብለዋል፡፡
የፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኖኤል ባሮት በበኩላቸው “በቀጠናው ተለዋዋጭ ከሆነው ሁኔታ ጋር አብሮ ለመጓዝ እና ቀጣይነት ያለው ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲሁም የሊባኖስን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ ምርጫው የመጀመሪያ እርምጃ ነው” ብለዋል፡፡
በፖለቲካ ፣ በጦርነት እና በማህበራዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኝውን ሀገር ከአመታት በኋላ በቋሚ መሪነት የሚረከበው ሰው ሀገሪቱን ማረጋጋት ላይ ትልቅ የቤት ስራ የሚጠብቀው ይሆናል፡፡
እስራኤል ካካሄደችው ጦርነት እና ከበሽር አላሳድ መውረድ ጋር በተያያዘ ቀጠናዊ ቅርጽ ለውጥ በታየበት ሁኔታ የተረጋጋ መንግስት መመስረት ፈተና ሊሆን እንደሚችልም ተነግሯል፡፡