ጀስቲን ትሩዶ ሊበራል ፓርቲ አዲስ መሪ እስከሚመርጥ ድረስ በስልጣን ላይ ይቆያሉ
ቀጣዩ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ሊሆን ይችላል?
ሰሜን አሜሪካዊቷ ካናዳ በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ሀገሪቱን ለዘጠኝ ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ጀስቲን ትሩዶ ከሰሞኑ ስልጣን እንደሚለቁ አሳውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ ስልጣን ለመልቀቅ የተገደዱት በሀገሪቱ የኑሮ ውድነት ለዜጎች ከባድ ሆኗል በሚለው ምክንያት ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የስደተኞች ጉዳይ ሌላኛው የሀገሪቱ ዋነኛ የፖለቲካ ትኩሳት መነሻ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ መንግስት ቁልፍ ሰው ናቸው የሚባሉት የፋይናንስ ሚኒስትር ስልጣን መልቀቅም ሶስተኛው ምክንያት እንደሆነ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ይህን ተከትሎም በካናዳ ያላቸው ተቀባይነት የተቀዛቀዘው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ፓርቲያቸው ሊበራል ፓርቲ ቀጣይ መሪውን እስከሚያሳውቅበት እስከ ቀጣዩ መጋቢት ወር ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ከዩክሬንዊ እናቷ በካናዳዋ አልቤርታ የተወለዱት እና የቀድሞዋ ጋዜጠኛ ቸርስቲያ ፍሪላንድ የጀስቲን ትሩዶ ዋነኛ ተተኪ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ካናዳን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት እና በገንዘብ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበሩት ፍሪላንድ የሊበራል ፓርቲ እና የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የቀድሞ የካናዳ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ማርክ ካርኔይ ሌላኛው የጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ ተተኪ እንደሚሆኑ ግምት አግኝተዋል፡፡
የ59 ዓመቱ ካርኔይ በካናዳ ያጋጠሙ የኢኮኖሚ ምስቅልቅሎችን ሊያስተካክሉ ይችላሉ የሚል ዕምነት የተጣለባቸው ሰው ሆነዋል፡፡
የወቅቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር አኒታ አናንድ፣ የሳይንስ እና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ፍራንሲ ፊሊፕ እና የወቅቱ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሜላኒን ጆሊ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን ሊረከቡ እንደሚችሉ የተገመቱ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡