የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን አፍሪካዊያን መሪዎችን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ቁጣ ቀሰቀሰ
ከሳህል ቀጠና የፈረንሳይ ጦር እንዲወጣ መደረጉን ተከትሎ “የአፍሪካ መሪዎች ምስጋና ቢሶች ናቸው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች ፕሬዝዳንቱ የሰጡት አስተያየት “ለአፍሪካ ያላቸውን ንቀት ያሳያል” በሚል ተቃውመዋል
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአፍሪካ መሪዎችን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ቁጣ ቀሰቀሰ፡፡
ፕሬዝዳንት ማክሮን የአፍሪካ ሀገራት የፈረንሳይ ጦር አማፂያን እና ታጣቂዎችን በመዋጋት ረገድ የዋለውን ውለታ አጣጥለዋል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
“የፈረንሳይ እገዛ ባይኖር ኑሮ የትኛውም የሳህል ቀጠና ሀገር ራሱን ከታጣቂዎች ተከላክሎ ሉአላዊ ሆኖ መቀጠል አይችልም ነበር፤ ሀገራቱ የፈረንሳይ ጦር ላደረገው ነገር ምስጋና ቢስ ሆነዋል” ነው ያሉት ማክሮን፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በፓሪስ በተካሄደው ዓመታዊ የአምባሳደሮች ጉባኤ ላይ ሲሆን፤ ፈረንሳይ በቀጠናው ያላትን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እቅዶችን እያደራጀች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቻድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዴራማን ኩልማላህ ለንግግሩ በሰጡት ምላሽ “የማክሮን አስተያየት ለአፍሪካ ያላቸውን ንቀት አሳይቷል” ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም “የፈረንሳይ መሪዎች የአፍሪካን ህዝብ ማክበር እና የከፈሉትን መስዋዕትነት ዋጋ መገንዘብ አለባቸው” ሲሉ በቴሌቪዝን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ቻድ ለ60 አመታት ከፈረንሳይ ጋር በነበራት አጋርነት ጊዜ ሀገሪቱ ካለመረጋጋት እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ስትታገል ፓሪስ የራሷን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ማሳደድ ላይ አተኩራ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የሴኔጋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኦስማን ሶንኮ በበኩላቸው ፈረንሳይ ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደ ሊቢያ ያሉ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትን በማተራመስ በነበራት አስተዋፅኦ የቀጠናውን ደህንነት አደጋ ላይ ጥላለች ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
አክለውም “ፈረንሳይ የአፍሪካን ደህንነት እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ አቅሙም ሆነ ህጋዊ ሰውነት የላትም” ነው ያሉት፡፡
በ2013 አማጽያንን ለመዋጋት እና ሰላም ለማስከበር ወደ ማሊ የተላኩት የፈረንሳይ ወታደሮች ከአንድ አመት በኋላ ተልእኮውን በማስፋ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶን ጨምሮ በሌሎች የቀጣናው ሀገራት ተሰማርተዋል፡፡
ባለፉት ሶስት አመታት በርካታ መፈንቅለ መንግስቶችን ባስተናገደው የምዕራብ አፍሪካ ቀጠና የፈረንሳይን ጨምሮ የሌሎች ምእራባውያን ሀገራት ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ ጫና እየደረሰባቸው ነው።
ቻድ፣ ሴኔጋል እና ኮትዲቮር በቅርቡ ከፈረንሳይ ጋር የነበራቸውን የጸጥታ ስምምነቶች አቋርጠዋል። ማሊ፣ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ደግሞ መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ የፈረንሳይ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ አዘዋል፡፡