ድል ባለ ሰርግ የተጋቡት የ100 እና የ96 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ጥንዶች
ጥንዶቹ በሰርጋቸው ምሽት በፈረንሳይ ፕሬዝዳንት በተዘጋጅ የእራት ግብዣ ላይ ታድመዋል
ጥንዶቹ “ፍቅር ለወጣቶች ብቻ አይደለም፤ እኛም የፍቅር ስሜቶች አሉን፤ ስንገናኝ ልባችን ይመታል” ብለዋል
የ100 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት አሜሪካዊው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አርበኛ የ96 ዓመቷን እጮኛቸውን ድል ባለ ሰርግ ማግባታቸው ተነግሯል።
አሜሪካዊው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አርበኛ ሃሮልድ ቴሬንስ እና ፍቅረኛቸው ዣን ስወርሊን በፈረንሳይ ኖርማንዲ በዲ-ዴይ የባህር ዳርቻዎች አቅራቢያ ጋብቻ ስነ ስርዓታቸውን የፈጸሙ ሲሆን፤ ጥንዶቹ ፍቅር ዘላለማዊ መሆኑን አረጋግጠዋል በሚል ተወድሰዋል።
የ100 ዓመት የእድሜ ሙሽራው ሃሮልድ ቴሬንስ የሰርጋቸውን እለት "በሕይወቴ ውስጥ ምርጡ ቀን" ሲሉ ገልጸውታል።
የ96 የእድሜ ባለጸጋዋ ሙሽሪት በበኩላቸው “ፍቅር ለወጣቶች ብቻ አይደለም፤ እኛም የፍቅር ስሜቶች አሉን፤ ስንገናኝ ልባችን ይመታል” ሲሉ ተናግረዋል።
ጥንዶቹ በፈረንሳይ የተከበረው 80ኛው ዲ.ዴይ የድል ቀን ላይ የሰርግ ስነ ስርዓታቸውን የፈጸሙ ሲሆን፤ በዓሉን ለማብር የወጡ ሰዎች ሙሽሮቹ ለጋብቻ ስነ ስርዓታቸው ወደ ከተማዋ ማዘጋጃ ሲሄዱ መልካም ምኞታቸውን ሲገልጹላቸው ታይተዋል።
ሙሽራው ሃሮልድ ቴሬንስ የጋቻ ስነ ስርዓታቸውን ከፈጸሙ በኋላ ባስተላለፉት መልእክትም፤ "ለሁሉም የሰው ልጆች ጥሩ ጤናን፤በዓለም ላይ ሰላም እና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን እንዲሁም የዩክሬን እና የጋዛ ጦርነት እንዲያበቃ እመኛለሁ” ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
የጋቻ ስነ ስርዓታቸውን የፈጸሙት የእድሜ ባለጸጎቹ ምሽት ላይ በፈረንሳይ ኤሊዝ ቤተ መንግስት ልዩ የሆነ የእራት ግብዣ ላይ መታደማቸውም ተነግሯል።
በእራት ግብዣው ላይም የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የሀገራት መሪዎች እና ተወካዮች እንደተገኙበት ነው የተነገረው።
በዚሁ ወቅትም ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን “ለአዲሶቹ ተጋቢዎች እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉ የደስታ መልእክት አስተላልፈዋል።