በደቡብ አፍሪካ 800 ጥንዶች በአንድ ላይ ተሞሸሩ
ጥንዶቹ ሰርጋቸውን ከአንድ በላይ ጋብቻ በሚፈቅደው ቤተ-ክርስቲያን አከናውነዋል
የጅምላ የጋብቻ ስርዓቱ በዓመት ሦስት ጊዜ ይካሄዳል
በደቡብ አፍሪካ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ በትልቅ የሰርግ ስነ-ስርዓት ከ800 የሚበልጡ ጥንዶች ጋብቻ ፈጽመዋል።
ዓለም አቀፉ የጴንጤ ቆስጤ ቅዱሳን ቤተ-ክርስቲያን በአንዳንድ የአፍሪካ ማህበረሰቦች የተለመደውን ከአንድ በላይ ጋብቻ ይፈቅዳል።
ቤተ-ክርስቲያኑ በፈረንጆች 1962 ከተመሰረተች ጀምሮ የጅምላ ስርዓቱ በዓመት ሦስት ጊዜ ይከናወናል የተባለ ሲሆን፤ በፋሲካ በዓል፣ በታህሳስ እንዲሁም በመስከረም እንደሚካሄድ ተነግሯል።
የእሁዱ ሰርግ ከጆሃንስበርግ በስተሰሜን 100 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ በሚገኘው የዓለም አቀፍ የጴንጤ ቆስጤ ቤተ-ክርስቲያን ተካሂዷል።
ሁለተኛ የሚያገቡ ሚስቶች በስነ-ስርዓቱ በድምቀት ያሸበረቁ ልብሶችን የለበሱ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ጊዜ ሙሽሮች ደግሞ ነጭ ልብሶችን ለብሰዋል
ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ አባላት ያሉት ቤተ- ክርስቲያኑ፤ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙት ትላልቅ ቤተ-ክርስቲያናት አንዱ ያደርገዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የሰርግ ስነ-ስርዓቱ በቤተ-ክርስቲያኑ አመራር ላይ ለረጅም ጊዜ ሲነሳ የቆየው ውዝግብ እፎይታ የሰጠ ነው ተብሏል።
በፈረንጆች 2016 የቤተ-ክርስቲያኑ መሪ ግላይተን ሞዲሴ ካለፉ በኋላ በሦስት ወንድማማቾች መካከል የመተካካት ጦርነቱ ተጀመሯል።