ከ1 ሺህ በላይ ሶሪያውን በኤርፖርት እስርቤት ውስጥ መገደላቸውን ሪፖርት አመላከተ
ድርጊቱ ተፈጽሞበታል በተባለው አውሮፕላን ማረፍያ አቅራቢያ 7 የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል

በበሽር አላስድ አስተዳደር ወቅት በከፍተኛ ስቃይ፣ የምግብ እና የህክምና እጦት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል
በበሽር አል አሳድ ዘመን ከ1000 በላይ ሶሪያውያን በወታደራዊ አውሮፕላን ማረፊያ እስር ቤት ውስጥ መሞታቸውን ሪፖርት አመላከተ፡፡
ከደማስቆ ወጣ ብሎ በሚገኝ ወታደራዊ ኤርፖርት በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በከፍተኛ ስቃይ፣ በድብደባ፣ በምግብ እና በህክምና እጦት እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች መገደላቸውን ሮይተርስ አገኘሁት ያለውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የሶሪያ ፍትህ እና ተጠያቂነት ማዕከል በታህሳስ ወር ፕሬዝደንት በሽር አል አሳድ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የጠፉ ሰዎችን እና የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለማጋለጥ ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በዚህም በደማስቆ አቅራቢያ በሜዚህ ከተማ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፍያ ታስረው ከተለቀቁ ምስክሮች ባሰባሰበው የምስክርነት ቃል፣ የሳተላይት ምስሎች እና ፎቶግራፎችን በመጠቀም መረጃዎችን ማሰበሰቡን እንዲሁም የመቃብር ስፍራዎችን መለየቱን አስታውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሴድናያ እስር ቤት ውስጥ የታሰሩ እና የጠፉ ሰዎች ማህበር 156 በህይወት የተረፉ እና 8 የቀድሞ የኤርፖርት ደህንነት አባላትን ምስክርነት ቃል ተቀብሏል፡፡
የሜዜህ ወታደራዊ አውሮፕላን ማረፊያ የአሳድ መንግስት የግድያ እና አስገድዶ መሰወሪያ ዋነኛ ማዕከል የነበረ ሲሆን ከ2011 - 2017 ድረስ ቢያንስ 29 ሺህ እስረኞች ይገኙበት እንደነበር ሪፖርቱ አመልክቷል።
ከሪፖርቱ አዘጋጆች አንዱ የሆነው ሻዲ ሀሮን በዚህ እስር ቤት ውስጥ ከታሰሩ ሰዎች መካከል ሲሆን፥ እ.ኤ.አ. ከ2011-2012 የተቃውሞ ሰልፎችን በማዘጋጀት ከተያዘ በኋላ የእምነት ቃል እንዲሰጥ በእስር ቤቱ ውስጥ በየቀኑ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ስቃይ በሚያስከትሉ ምርመራዎች ውስጥ ማለፉን ገልጿል።
ሻዲ ሀሮን ከሮይተርስ ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ “በየቀኑ በምርመራ የሚሰቃዩ ሰዎችን ድምጽ እንሰማለን፤ በየሁለት ቀኑ ደግሞ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች ከእስር ቤቶች ውስጥ እየወጡ ሲገደሉም አይተናል፤ በስፍራው የነበረን ቆይታ ሞትን የሚያስመኝ ነበር” ሲል ተናግሯል፡፡
በተጨማሪም “ከከፍተኛ አካላዊ ድብድባ እና ስቃይ በኋላ ለቀናት አንዳንድ ጊዜም ለሳምንታት ያልታከሙ ሰዎች በየስፍራው ሞተው መመልከት የተለመደ ነገር ነበር” ሲል የቀድሞው ታሳሪ አብራርቷል፡፡
የሶሪያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ ደማስቆ ከአሳድ አስተዳደር ነጻ ከወጣች ጀምሮ ቀደም ሲል በእስር ላይ የሚገኙ ቁጥራቸው 100 ሺ የሚጠጉ ሰዎች እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም፡፡
አሁን ይፋ በተደረገው ሪፖርት የሟቾች ቁጥር አንድ ሺህ እንደሆነ ቢገለጽም በኤርፖርቱ ውስጥ የሚሞቱ ሰዎች የሚቀበሩባቸው ተጨማሪ የጅምላ መቃብሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡