እስራኤል ደቡባዊ ሶሪያ ከጦር ነጻ ቀጣና እንዲሆን እንደምትፈልግ ገለጸች
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ በቦታው ያለውን ለመከላከል የሚያስችል ምሽግ ይዛ ትቆያለች ብለዋል

ኤችቲኤስ በፈጸመው መብረቃዊ የበሽር አላሳድ አስተዳደር መገርሰሱን ተከትሎ እስራኤል በሶሪያ ውስጥ በሚገኘው ተመድ በሚቆጣጠረው ከጦር ነጻ ቀጣና ኃይሏን አሰማርታለች
እስራኤል ደቡባዊ ሶሪያ ከጦር ነጻ ቀጣና እንዲሆን እንደምትፈልግ ገለጸች።
እስራኤል በደቡብ ሶሪያ የሀያት ታህሪር አልሻም(ኤችቲኤስ) ወይም ለሀገሪቱ መሪዎች ቅርበት ያላቸውን ኃይሎች እንቅሰቃሴ እንደማትታገስና ቦታው ከጦር ነጻ ቀጣና(ዲሚሊታራይዝድ) እንዲሆን እንደምትፈልግ በትናንትናው እለት ገልጻለች።
የቀድሞው የአልቃ ኢዳ አጋር የነበረው ኤችቲኤስ ሌሎች ሌሎች ታጣቂ ኃይሎችን በማስተባበር በፈጸመው መብረቃዊ ጥቃት ለ24 አመታት ሶሪያን የመራውን የበሽር አላሳድ አስተዳደር መገርሰሱን ተከትሎ እስራኤል በሶሪያ ውስጥ በሚገኘው ተመድ በሚቆጣጠረው ከጦር ነጻ ቀጣና ኃይሏን አሰማርታለች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ በቦታው ያለውን ለመከላከል የሚያስችል ምሽግ ይዛ ትቆያለች ብለዋል።
"የኤችቲኤስ ሆነ የአዲሱ የሶሪያ ጦር ኃይሎች ከደማስቆ ደቡባዊ አቅጣጫ ባሉ ቦታዎች እንዲሰማሩ አንፈቅድም። በደቡብ ሶሪያ ያሉ ኩይትራ፣ዳራና ስዌዲያ የተባሉ ግዛቶች ሙሉ በሙሉ ከጦርነት እንቅስቃሴ ነጻ እንዲሆኑ እንፈልጋለን" ሲሉ ኔታንያሁ በወታደር ምረቃ ስነስርዓት ላይ ተናግረዋል።
ኔታንያሁ አክለውም በደቡብ ሶሪያ በዱሬዝ አናሳ የሀይማኖት ተከታዮች ላይ የሚደረግን ጥቃት አንታገስም ብለዋል።
ሶሪያ የእስራኤል ጦር ከግዛቷ እንዲወጣ እየተጠየቀች ነው። ተመድ እስራኤል የሶሪያን ድንበር በመጣስ አለምአቀፍ ህግ መጣሷን ገልጾ ወታደሮቿን እንድታስወጣ አሳስቧል።