ፑቲንና የሶሪያ ፕሬዝዳንት አል ሻራ ለመጀመሪያ ጊዜ መነጋራቸው ተሰማ
አል ሻራ እና ፑቲን ከበሽር አል አሳድ መንግስት መውደቅ በኋላ በቀጥታ ሲገናኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/13/252-121500-whatsapp-image-2025-02-13-at-11.14.07-am_700x400.jpeg)
ሩሲያ የሶሪያ ቀድሞ የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ጥገኝት እንደሰጠች መነገሩ ይታወሳል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከአዲሱ የሶሪያ የሽግግር መንግስት ፐሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ መነጋራቸው ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንት ፑቲንና የሶሪያ ፕሬዝዳንት አል ሻራ የመጀመሪያ ውይታቸውን በስልክ እንዳደረጉም የሶሪያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫው አስታውቋል።
በውይይቸውም አል-ሻራ "በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ያነሱ ሲሆን፤ ሶሪያን ህዝብ ጥቅም በጠበቀ መልኩ እንዲሁም የሶሪያን መረጋጋት እና ደህንነትን ማጠናከር ላይ ሀገራቸው ከሁሉም ወገኖች ጋር ለመስራት በሯ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፑቲን የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ አል-ሻይባኒ ሩሲያን እንዲጎበኙ ይፋዊ ግብዣ ማቅረባቸውን የሶሪያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
"የሩሲያ የሶሪያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንደምትደግፍ በውይይቱ ላይ መነሳቱን ክሬምሊን ባወጣው መግለጫው አስታውቋል።
በአል ሻራ የሚመራው ሃያት ታህሪር አል ሻም ቡድን የሩሲያ የቅርብ አጋር የነበሩትን የቀድሞ የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድን ባሳለፍው ታህሳስ ወር ከስልጣን ማስወገዱ ይታወሳል።
የሞስኮ የቅርብ አጋር የነበሩት በሽር አል አሳድ ከስልጣን መወደጋቸውን ተከትሎ በሶሪያ የሚገኙ ሁለት የሩሲያ ወታደራዊ ጣያዎች እጣ ፈንታ ጥያቄ ሲነሳበት መቆየቱም ይታወቃል።
ሩሲያ የበሽር አል አሳድ መንግስት በስልጣን ላይ እንዲቆይ ድጋፍ ስታደርግ የቆየች ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2015 የአማጽያን ይዞታዎች ላይም ከባባድ የአየር ድብደባዎችን ፈጽማለች።
የሶሪያ አማጽያን ባሳለፍው ታህሳስ ወር ላይ ደማስቆን ሲቆጣጠሩም ሩሲያ ለቀድ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ጥገኝነት የሰጠች ሲሆን፤ ይህም አዳዲሶቹን የሶሪያ መሪዎችን ጨምሮ በርታ የሀገሪቱ ዜጎች አስቆጥቷል።