ቱርክ እና ሶሪያ የመከላከያ አጋርነት ስምምነት ሊፈጽሙ ነው
አንካራ አዲሱን የደማስቆ አስተዳደር በመልሶ ግንባታ እና በወታደራዊ ስልጠና ማገዝ እንደምትፈልግ አስታውቃለች
በዛሬው ዕለት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ይህን የመከላከያ አጋርነት ስምምነት እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል
የሶሪያ የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ እና የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶሀን በዛሬው ዕለት በአንካራ የጋራ የመከላከያ አጋርነት ስምምነት እንደሚፈጽሙ ይጠበቃል፡፡
ስምምነቱ ቱርክ በማዕከላዊ ሶሪያ የአየር ሀይል የጦር ሰፈር እንድታቋቁም እና በምላሹ የሶሪያ ወታደሮችን ማሰልጠንን የሚያካትት ነው፡፡
ሮይተርስ ስለስምምነቱ ከሚያውቁ የጸጥታ እና የደህንነት ባለስልጣናት ምንጮች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት የሶሪያ የሽግግር መንግስት መሰል ወታደራዊ አጋርነት ስምምነት ሲፈጽም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
በዚህም መሰረት ቱርክ በሶሪያ ሁለት አዳዲስ የአየር ጦር ሰፈር እንድትመሰርት፣ የሶሪያን የአየር ክልል ለወታደራዊ አገልግሎት እንድትጠቀም እና በሶሪያ አዲስ ጦር ውስጥ ወታደሮችን በማሰልጠን ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እንድትጫወት እንደሚያስችላት ምንጮቹ ጠቁመዋል።
የኔቶ አባል የሆነችው ሀገር የበሽር አላሳድን መንግስት የጣሉትን ተዋጊዎች በፖለቲካ እና በተለያዩ መንገዶች ስትደግፍ መቆየቷ ይታወቃል፡፡
አንካራ ራሷን በአዲሷ ሶሪያ ውስጥ የአሳድ ዋና ቀጣናዊ ደጋፊ ኢራን መገፋትን ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት እና በቀጠናዊ ወሳኝ ተዋናይ ስፍራ ላይ ለመቀመጥ በፍጥነት እየተንቀሳቀሰች ነው ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህ የቱርክ የተጽዕኖ ፈጣሪነት ፈጣን እንቅስቃሴ ከባህረ ሰላጤው አረብ ሀገራት ጋር ፉክክር እንዲፈጠር ሊያደርግ እንደሚችል ዘገባው አክሏል፡፡
ከአሳድ ውድቀት በኋላ የሶሪያ አዲሱ አመራር ሰራዊቱን እና የተለያዩ አማፂ ቡድኖችን በትኖ ወደ አዲስ ወታደራዊ እዝ ውስጥ ለማዋሃድ እየሰራ ነው።
ከአንካራ ጋር ይፈጸማል በተባለው የመከላከያ ስምምነት መሰረት ሁለቱ ሀገራት በጋራ ወታደራዊ ስምሪቶች ዙሪያ ሊተባበሩ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
ደማስቆ እና አንካራ በቅርበት ይሰሩበታል የተባለው ሌላኛው ጉዳይ መልሶ ግንባታን የተመለከተ ይሆናል፡፡
የቱርክ ፕሬዝዳንት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ፋህረቲን አልቱን ኤርዶሀን እና አልሻራ በሶሪያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ የሶሪያን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት፣ መረጋጋት እና ደህንነትን ለማስፈን በሚያስችሉ የጋራ እርምጃዎች ላይ ይወያያሉ ብለዋል ።