በ2024 104 ጋዜጠኞች ተገድለዋል፤ ግማሾቹ በጋዛ ነው ህይወታቸው የተቀጠፈው
እስያ ከመካከለኛው ምስራቅ በመቀጠል ለጋዜጠኞች አደገኛው ቀጠና ነው ብሏል አለማቀፉ የጋዜጠኞች ፌደሬሽን

የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ 138 ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች መገደላቸው ተገልጿል
ሊጠናቀቅ 21 ቀናት ብቻ የቀሩት 2024 የበርካታ ጋዜጠኞች ህይወት ያለፈበት አመት ሆኗል።
የአለማቀፉ የጋዜጠኞች ፌደሬሽን (አይኤፍጄ) በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ በ2024 104 ጋዜጠኞች መገደላቸውን አመላክቷል።
በአለማቀፍ ደረጃ በ2024 ከተገደሉት ውስጥ ግማሾቹ እስራኤል በጋዛ ከሃማስ ጋር ለምታደርገው ጦርነት ሽፋን ሲሰጡ የነበሩ ናቸው ብሏል ፌደሬሽኑ።
የተገደሉት ጋዜጠኞች ቁጥር ከ2023ቱ በ25 ዝቅ ቢልም በርካታ ጋዜጠኞች የተገደሉበት አመት ነው ብለዋል የፌደሬሽኑ ዋና ጸሃፊ አንቶኒ ቤላገር ከአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቆይታ።
እስራኤል በጋዛ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች 55 ፍልስጤማውያ የሚዲያ ሰራተኞች በ2024 መገደላቸውንም ጠቁመዋል።
ቤላገር ከጥቅምት 2023 ወዲህ 138 ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች መገደላቸውን በመጥቀስም "አለም እያየው የተፈጸመውን ግድያ አጥብቄ አወግዛለሁ" ብለዋል።
በጋዛው ጦርነት በርካታ ጋዜጠኞች ኢላማ ተደርገው ጥቃት እንደተፈጸመባቸውና አንዳንዶቹም በተሳሳተ ስፍራ እና ጊዜ ራሳቸውን ጦርነት ውስጥ አግኝተውት ህይወታቸው ማለፉን አብራርተዋል።
እስያ ከመካከለኛው ምስራቅ በመቀጠል ለጋዜጠኞች ደህንነት አደገኛው ቀጠና ነው ተብሏል።
በእስያ በ2024 20 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ ፓኪስታን ስድስት፣ ባንግላዲሽ አምስት፣ ህንድ ደግሞ ሶስት ድርሻ አላቸው።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሊጠናቀቅ ሶስት ሳምንት በቀረው የፈረንጆቹ አመት የአራት ጋዜጠኞችን ህይወት መቀማቱ ተገልጿል።
የአለማቀፉ የጋዜጠኞች ፌደሬሽን (አይኤፍጄ) የተለየ አቆጣጠር ስልት ስለሚጠቀም የሚያወጣው አሃዝ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ይፋ ከሚያደርገው ሲልቅ ይታያል።
ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን በ2023 54 ጋዜጠኞች መገደላቸውን መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፥ የዚህ አመት ሪፖርቱን በሳምንቱ መጨረሻ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
የአለማቀፉ የጋዜጠኞች ፌደሬሽን (አይኤፍጄ) በ146 ሀገራት ውስጥ የሚገኙ የ187 ድርጅቶች ከ600 ሺህ በላይ የሚዲያ ሰራተኞችን የሚወክልና ለመብታቸው የሚከራከር ተቋም ነው።
ፌደሬሽኑ ከፈረንጆቹ 1953 ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋዜጠኞችን ወክሎ ይቀርባል።