ስማርት ስልክን ለአንድ ወር ባለመጠቀም ብቻ 10 ሺህ ዶላር የሚያሸልመው ውድድር
የአሜሪካው እርጎ አቅራቢ ኩባንያ ሲጂ በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎችን እየመዘገበ ነው
አሜሪካውያን በቀን በአማካይ 5 ስአት ከ25 ደቂቃዎችን ስልካቸው ላይ ያጠፋሉ
በቀን ስንት ጊዜ ስማርት ስልክዎን ይመለከታሉ? ቀኑን ሙሉ ስልክዎ ከእጅዎ ቢጠፋ ምን አይነት ስሜት ይሰማዎታል?
ለ30 ቀናት ስልክዎን ከጎንዎ አርቀው 10 ሺህ ዶላር ይሸለማሉ ቢባሉስ ምን ይላሉ?
የአሜሪካው ታዋቂ እርጎ አቅራቢ ኩባንያ “ሲጂ ዲያሪ” በዲጂታሉ አለም የሚደርስ መረበሽን የሚያስቀር ውድድር ማዘጋጀቱን አስታውቋል።
ከ311 ሚሊየን በላይ ሰዎች ስማርት ስልክ ተጠቃሚ ባለባት አሜሪካ እያንዳንዱ ሰው በቀን በአማካይ 5 ስአት ከ25 ደቂቃዎችን ስማርት ስልኩ ላይ እንደሚያጠፋ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ይህም ማህበራዊ መስተጋብርን እያጠፋ ለተለያዩ የጤና እክሎች እየዳረገ እንደሚገኝም ተደጋግሞ ይነሳል።
“ሲጂ ዲያሪ” ያዘጋጀው “ከዲጂታሉ አለም የመንጻት ውድድር”ም ለጉዳዩ ትኩረት ለመስጠት ያለመ ነው ተብሏል።
ውድድር ለመሳተፍ ስማርት ስልካቸውን ለአንድ ወር የሚዘጉ ሰዎች እያንዳንዳቸው 10 ሺህ ኮች ላይ እን ለአንድ ወር ከራቁ ሽልማት እሰጣለሁ ብሏል።
“ብዙ መረበሽ የሌለበት ቀላል ህይወት መኖር ያለውን ፋይዳ በአግባቡ እንረዳለን፤ አሁን ላይ ኑሯችን እየረበሹ ከሚገኙ ጉዳዮች ስልኮቻችን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ” የሚለው ኩባንያው፥ ከዚህ ቀደምም ለአንድ ወር አልኮል ያለመጠጣት ውድድር ማካሄዱ ይታወሳል።
ኩባንያው ለአንድ ወር ስልካቸውን መጠቀም ለማቆም የወሰኑ ሰዎች ማመልከቻቸውን እስከ ጥር መጨረሻ እንዲያስገቡ የጠየቀ ሲሆን፥ አሳማኝ ማመልከቻ ያስገቡ 10 ተወዳዳሪዎች ይመረጣሉ ብሏል።
አስሩም ተወዳዳሪዎች ስልካቸውን ኩባንያው በሚያቀርብላቸው የማይከፈት ሳጥን ውስጥ ያስቀምጣሉ የተባለ ሲሆን፥ ለውድድሩ ካቀረቡት ስማርት ስልክ ውጭ ሌላ ስልክ እንደሌላቸው ተረጋግጦ ክትትል እንደሚደረግባቸውም ተገልጿል።
በውድድሩ አሸናፊ የሆኑት ከ10 ሺህ ዶላሩ ባሻገር ሌሎች ሽልማቶች ይሰጣቸዋል መባሉንም ዩናይትድ ፕረስ ኢንተርናሽናል ዘግቧል።
ሽልማቱ የሚያጓጓ ቢመስልም ከስማርት ስልክ ለወር አይደለም ለአንድ ቀን መራቅ የሚከብዳቸው በርካታ ናቸው።