የስማርት ስልኮች ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ6 ቢሊየን በላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ
የስማርት ስልክ ሱሰኛ መሆንዎን በቀላሉ እንዴት ማወቅ ይችላሉ?
በ2022 ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ስማርት ስልኮች የተሽጡ ሲሆን፥ አጠቃላይ የስማርት ስልኮች ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከ6 ቢሊየን በላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚሁ አመት የተደረጉ ጥናቶችም የስማርት ስልኮች እና የተጠቃሚዎቻቸውን አስደንጋጭ አሃዛዊ ትስስር አሳይተዋል
ስማርት ስልክዎ አጠገብዎ ከሌለ መተኛት ይከብድዎታል? የባትሪው መቀነስስ ጭንቅ ውስጥ ይከትዎታል? ስልክዎ ሳይጠራ የተደወለልዎ፥ መልዕክት ሳይላክልዎ መልዕክት መላኩን የሚያሳውቅ ድምጽ ሰምተው ስልክዎን ደጋግመው አይተዋል? መልስዎ አዎ ከሆነ የስማርት ስልክ ሱስ ተጠቂ ሳይሆኑ አልቀረምና ቆም ብለው ያስበቡብት።
በ2022 ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ስማርት ስልኮች ተሽጠዋል። የስማርት ስልኮች ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከ6 ቢሊየን በላይ መድረሱ ይነገራል። ይህ አሃዝ በ2016 ከነበረበት በ49 በመቶ ማደጉ የስማርት ስልኮችን ተፈላጊነት ያሳያል።
ከተጠቃሚው ቁጥር መጨመር እኩል በስማርት ስልክ ሱስ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ቁጥርም እያደረ እየጨመረ መሆኑን ፔው የተሰኘው የጥናት ተቋም ያወጣው የዳሰሳ ጥናት ያመለክታል።
በአሜሪካ 47 ከመቶ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ስልካቸውን የሙጥኝ ያስባለ ሱስ እንደያዛቸው ያምናሉ።
71 ከመቶው የሚሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎችም ከፍቅር ጓደኛቸው ጋር ከሚያሳልፉት ጊዜ በበለጠ ለስልካቸው ጊዜ እንደሚሰጡ ነው የተናገሩት።
በጥናቱ ምላሽ ከሰጡት ህጻናት ውስጥም ሁለት ሶስተኛው በቀን ከ4 ስአታት በላይ በስልካቸው እንደሚያጠፉ ተመላክቷል።
ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተሳታፊዎች ስልካቸውን ሳይዙ መንቀሳቃስ ከፍተኛ የመረበሽ ስሜትና ፍርሃት ውስጥ እንደሚከታቸው የተናገሩ ሲሆን፥ ስማርት ስልኮችን እየተጠቀሙ መንዳት ከሚደርሱ አደጋዎች 20 በመቶውን ይሸፍናል ተብሏል።
የስማርክ ስልክ ሱስ በተጠቃሚው የእለት ለእለት የህይወት ኡደት፣ የስራ ውጤታማነትና የማህበራዊ ህይወት ላይ እያደረስ ያለው ጉዳትም ከፍተኛ ስለመሆኑ ይነገራል።
ቀጣዮቹ አስደንጋጭ ቁጥሮችም የስማርክ ስልክ ተጠቃሚዎች ችላ ብለው ካለፏቸው በያዙት ስልክ ሱስ ተጠልፈው መውደቃቸውን ያሳያል ይላሉ ባለሙያዎች።
- በየቀኑ በአማካይ ከ150 ጊዜ በላይ የተዘጉ (በፓተርን የተቆለፉ) ስልኮች ይከፈታሉ
- የሞባይል ስልኮችን ስክሪኖች በቀን ከ2 ሺ 600 ጊዜ በላይ ይነካካሉ
- ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ባትሪ ካልዘጋባቸው በስተቀር ስልካቸውን አያጠፉም
- ከ70 በመቶ በላይ ተጠቃሚዎች ስልካቸውን አጠገባቸው አድርገው ይተኛሉ፥ ከነዚህ ውስጥ ሶስት በመቶው ስልካቸውን በእጃቸው እንደያዙት ያንቀላፋሉ
- እድሜያቸው ከ10 እስከ 12 ከሚሆኑት አሜሪካውያን ህጻናት 45 ከመቶው ስማርት ስልክ አላቸው
- ከአሜሪካውያን ታዳጊዎች 80 በመቶው፤ በብሪታንያ 63 በመቶው ፤ በጃፓን 61 በመቶው በሰአት ከአንድ ጊዜ በላይ ስልካቸውን የመነካካት ባህሪ አዳብረዋል
- የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች በቀን በአማካይ 58 ደቂቃ ፌስቡክ ላይ 53 ደቂቃ ደግሞ ኢንስታግራም ላይ ያሳልፋሉ
- የቲክቶክ ተጠቃሚዎች በቀን በአማካይ 52 ደቂቃዎችን አጫጭር ቪዲዮዎችን በማየት ያሳልፋሉ (በሳምንት ከስድስት ስአት በላይ እንደማለት ነው)
- ሰራተኞች በቀን በአማካይ 2 ስአት ስልካቸውን በመጠቀም ስራ ይበድላሉ
- በብሪታንያ 58 በመቶ ሰራተኞች በመስሪያ ቤቶች የተቆለፉ ድረገጾችን ስብሮ ለመግባት ስማርት ስልካቸውን ይጠቀማሉ
ስማርት ስልኮች አሰራራቸው በራሱ ሱስ ውስጥ የሚከት ነው የሚለው የአሜሪካ አዲክሽን ሴንተር ድረገጽ፥ የየእለት እንቅስቃሴያችን ከስልካችን ጋር የተያያዘ መሆኑን ያወሳል።
መዝናኛው፣ መረጃ መሰብሰቢያው፣ ክፍያ መፈጸሚያው፣ አቅጣጫ ጠቋሚው፣ አማካሪው ስማርት ስልክ አጠቃቀሙ ገደብ ካልተበጀለት ግን ጉዳቱ እያመዘነ መሄዱ አይቀርም።
ከመጠን ያለፈና በሱስ ደረጃ የተቀመጠ የስማርት ስልክ አጠቃቀም የሰነልቦና ባለሙያዎች ከአዳዲስ ስያሜዎች ጋር እንዲያስተዋውቁን አድርጓል።
ከነዚህም ውስጥ “ኖሞፎቢያ” (ስልክ የሌለበትን ሁኔታ መፍራት) ፣ ቴክስታፍሪኒያ (መልዕክት ሳይገባልን ግን የተላከልን መስሎን የማየት ልማድ) እና ፋንተም ቫይብሬሽን (ስልካችን በስህተት የነዘረን መስሎን አውጥተን የምናይበት) የተሰኙት ይገኙበታል።
እናም እነዚህ ምልክቶችን ደጋግማችሁ ከተመለከታችሁ በስማርት ስልካችሁ ሱስ ውስጥ ተዘፍቃችሁ ሊሆን ስለሚችል ባለሙያዎችን አማክሩ።
የድብርት፣ እንቅልፍ እጦት እና የስራ መጥላት ባህሪ እየተላመደ መሄድም ከማህበራዊ ህይወት ከመራቅ ጋር ተዳምሮ ራስን ወደማጥፋት ሊያመራ ይችላል፤ ጥናቶችም ይህንኑ አሳይተዋል የሚሉት የስነልቦና ባለሙያዎች ጉዳዩን እንደቀላል ነገር መመልከት እንደማይገባም ያሳስባሉ።