የስማርት ስልክ አጠቃቀማችን ጤናማ የሚያደርጉ መተግበሪያዎችን መጠቀም ውድ ጊዜያችን ይታደጋል
ስማርት ስልኮች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን አካል ከሆኑ ሰነባብተዋል።
ውሏችን ያለስማርት ስልክ ምን እንደሚመስል ለማሰብ እንኳን የሚከብደን ጥቂት አይደለንም።
ይሁን እንጂ ከእጃችን የማይጠፉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ትሩፋት ብቻ ሳይሆን ፈተናም ይዘው ነው አብረውን ውለው የሚያድሩት።
በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እያንዳንዱ የስማርት ስልክ ተጠቃሚ በቀን በአማካይ 4 ስአት ከ30 ደቂቃዎችን ስልኩ ላይ ያጠፋል። ይህ አማካይ በስልክ ስናወራ የምናጠፋውን ጊዜ አይጨምርም ይላል የስታስቲካ መረጃ።
የስማርት ስልኮችን የሙኝኝ ብለን የምናጠፋው ጊዜ ዘርፈብዙ የጤና ችግሮችን እያስከተለ እንደሚገኝ በተለያየ ጊዜ የወጡ ጥናቶች ያሳያሉ።
እናም የስማርት ስልክ አጠቃቀማችን የሚከታተሉ፣ አሃዛዊ መረጃ እያቀበሉ ምክረሃሳቦችን የሚጠቁሙ እንዲሁም በጊዜ ገደብ እንድንጠቀም የሚፈቅዱ መተግበሪያዎችን መጠቀም የቴክኖሎጂ ውጤቶቹ ከደቀኑብን ፈተና በጥቂቱም ቢሆን ለመውጣት ያግዛል።
ቀጥለው የቀረቡት 7 መተግበሪያዎችም የስማርት ስልክ አጠቃቀማችን ለመቆጣጠርና ለመገደብ ያስችላሉ።
1. Forest
ይህ መተግበሪያ የስማርት ስልክ አጠቃቀማችን ጨዋታ በመሰለ ቁምነገር ነው እንድናስተካክል የሚያግዘን። አረንጓዴ ገጽታ ያለው “ፎረስት” መተግበሪያ ስልካችን መጠቀም ስንጀምር የዛፍ ዘር ሲዘራ ያሳያል፤ ከጥቂት ቆይታ በኋላም ፍሬው ማደግ ይጀምራል፤ የዛፍ መልክ እየያዘም ይሄዳል። በዚህ መተግበሪያ አጠቃቀማችን እንዲገደብ ያደረግናቸው (እንደ ፌስቡክና ቲክቶክ ያሉ መተግበሪያዎችን) ከልክ በላይ መጠቀም ስንጀምር ግን ዛፉ እየጠወገ ሄዶ ይወድቃል። በጣም ለረጅም ስአት ስልካችን ላይ ስናጠፋም “ፎረስት” ስልካችን እንዲዘጋ ያደርጋል።
የስማርት ስልክ አጠቃቀማችን ከተፈጥሮ ጋር ያሰናሰለው ይህ መተግበሪያ በቀላሉ የሚያነቃና ፈጣን ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑ ተነግሮለታል።
2. SPACE
“ስፔስ” የስማርት ስልካችን አጠቃቀም በመቆጣጠር ጊዜያችን የሚበሉትን የሚጠቁመን ሁነኛ መተግበሪያ ነው። ረጅም ስአት የምንጠቀመውን መተግበሪያ ማወቅ ለመፍትሄው አንድ እርምጃ ለመጓዝ ያስችላል።
ይህ መተግበሪያ ፌስቡክ ወይንም ቲክቶክ በቀን ውስጥ በምንፈልገው መጠን ገደብ አስቀምጠን እንድንጠቀም ያስችላል፤ ቀኑን ሙሉ ልንጠቀማቸው የማንፈልጋቸውንም መርጠን መዝጋት የሚያስችል አማራጭ አለው።
በተጨማሪም በቀናት ውስጥ የአጠቃቀም መሻሻል ወይንም ክፍተትን የሚያመላክት ዘርዘር ያለ ሪፖርት ይሰጠናል።
3. one sec
የአንድ ሰከንድ የማሰቢያ ጊዜ የሚሰጠው “one sec” መተግበሪያ የስልካችን ስክሪን ላይ የምናጠፋውን ጊዜ ለመገደብ ትልቅ ድርሻ ካላቸው መተግበሪያዎች ይመደባል።
በዚህ መተግበሪያ ጊዜያችን የሚበሉ ናቸው ብለን የለየናቸውን መተግበሪያዎች ካስገባን ልንከፍታቸው ስንሞክር “እስኪ አስብበት፤ ትንፋሽ ሰብስብ” የሚል መልዕክት ይደርሰናል። ይህቺ የአንድ ሰከንድ የማሰቢያ ጊዜ አጭር ብትመስልም ግዙፍ የሰነልቦና ተጽዕኖ እንዳላት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
4. AppBlock
“አፕብሎክ” ስያሜውም እንደሚያመላክተው ከልክ በላይ እየተጠቀምናቸው ያሉ መተግበሪያዎችን ለመዝጋት የሚውል ነው። በስልካችን ውስጥ ያሉ እያንዳንዱን መተግበሪያ አጠቃቀም መረጃ በመሰብሰብ እያዘናጋን ያለውን መተግበሪያ ቢዘጋ መልካም ነው የሚል ምክረሃሳብ ያቀርባል። በዚህም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማገድ አልያም የምንጠቀምበትን የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ ያስችላል።
“አፕብሎክ” በስራ ስአት ስልካችን ደጋግመን የሚያስነሱ (የኢሜል፣ የተለያዩ መልዕክቶች ማሳወቂያ እና ማስታወሻዎች)ን ጨምሮ የስራ ውጤታማነታችን የሚቀንሱ መተግበሪያዎችን እንድንገድባቸው ያስችላል።
5. OffScreen
ይህ መተግበሪያ የስልካችን ስክሪን ለምን ያህል ጊዜ እንደበራና ምን አይነት መተግበሪያዎች እንደተከፈቱ እየተከታተለ አይናችን ብሎም ጠቅላላ ጤናችን የሚታደጉ እርምጃዎችን እንድንወስድ ያግዘናል።
ስልካችን በምን ያህል ደቂቃ ልዩነት ማንሳትና መጠቀም እንዳለብን መወሰን የሚያስችለን “OffScreen” በአፍቅሮተ ስማርት ስልክ ስለመውደቃችን አመላካች መረጃ ያቀብለናል።
6. ScreenZen
“ScreenZen” ልክ እንደ “one sec” ለረጅም ጊዜ የምንጠቀማቸውን መተግበሪያዎች ስንከፍት የማሰቢያ ጊዜ ይሰጠናል፤ ጊዜያችን የሚበሉ መተግበሪያዎች በፍጥነት እንዳይከፍቱም እየተሽከረከረ ሰልችቶን እንድንመለስ ያበረታታል። ይህ መተግበሪያ የማህበራዊ ትስስር ገጾች አጠቃቀማችን በጊዜ ገደብ እንድንወስንና አፈጻጸሙንም ራሳችን በራሳችን እንድንገመግም እድል ይፈጥራል።
7. Engross
ስማርት ስልካችሁ በስራ ቦታ ክፉኛ የሚፈታተናችሁ፤ ቀልባችሁን ከመሰብሰብ ይልቅ የሚበታትንባችሁ ከሆነ “Engross” መፍትሄ አለው ተብሏል። መተግበሪያው በቢሮ ውስጥ በየእለቱ የምንከውናቸውን ስራዎች በስአት ከፋፍለን እንድናስቀምጥ ማስቻሉና በተቀመጠው ገደብ ስራችን መጠናቀቁን መከታተሉ ሙሉ ትኩረታችን ስራችን ላይ እንዲሆን ያደርጋል።
የስማርት ስልኮች የህይወታችን አካል እንደመሆናቸው እርግፍ አርገን ልንተዋቸው የምንችልበት ጊዜ አይደለም።
ይሁን እንጂ ስልኮቻችን ህይወታችን የሚያቀሉ እንጂ የጤናችን ጸር እንዲሆኑ መፍቀድ ተገቢ አይደለም።
ብዙዎች ከገቡበት የስማርት ስልክ ሱሰኝነት ለመውጣት ፈተና እንደሆነባቸው የሚገልጸው ቢዝነስ ኢንሳይደር፥ ከላይ የተጠቀሱት ሰባት መተግበሪያዎች የሚያጋሩን መረጃ አስደንጋጭና አስተማሪ በመሆኑ እንሞክራቸው ዘንድ መክሯል።