ከህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ጋር በተያያዘ ከ11 ሺህ በላይ የኮቪድ-19 ናሙናዎች ምርመራ መደረጉ ተገለጸ
በጉባኤው ለመሳተፍ ወደ አፍሪካ ህብረት ግቢ ለሚገቡ ተሳታፊዎች ሁሉ በየዕለቱ ምርመራ እየተካሄደ ነው
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ በመካሄድ ላይ ይገኛል
ከአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ ጋር በተያያዘ ከ11 ሺህ በላይ የኮሮና ቫይረስ ናሙናዎች መመርመራቸው ተገለጸ፡፡
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አፍሪካ ህብረት ግቢ ለሚመጡ ተሳታፊዎች ሁሉ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የአፍሪካ ፕሬዝዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ በጉባኤው ላይ ለሚሳተፉት ሁሉ በየዕለቱ የኮሮና ቫይረስ ናሙና እየተወሰደ ውጤታቸው ‘ነጌቲቭ’ ወይም ቫይረሱ ያልተገኘባቸው ሰዎች ብቻ ወደ ስብሰባ አዳራሽ እንዲገቡ እየተደረገ ነው፡፡
ምርመራው የአፍሪካ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል ከኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ፣እንግዶች በሚያርፉባቸው ሆቴሎች እና በአፍሪካ ህብረት መግቢያ አምስት ቦታዎች ላይ በመከናወን ላይ መሆኑን አል ዐይን በቦታው ተመልክቷል፡፡
በአፍሪካ ህብረት አምስት ቦታዎች እየተካሄደ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ሲያስተባብሩ ያገኘናቸው እና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የድንገተኛ አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ሚኪያስ ተፈሪ ምርመራውን በፍጥነት ለተሳታፊዎች በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ከተጀመረ አንስቶ በየዕለቱ ፈጣን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በማድረግ ላይ ነን ያሉት ዶክተር ሚኪያስ እስካሁንም በአፍሪካ ህብረት ግቢ ውስጥ ባለው የምርመራ ጣቢያ ብቻ ከ11 ሺህ በላይ ናሙናዎች መመርመራቸውን ገልጸዋል፡፡
ለህብረቱ ጉባኤ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ እንግዶች አስቀድመው ፒሲአር ወይም የግለሰቦቹ የኮሮና ቫይረስ ሁኔታ የሚገልጽ የረጅም ጊዜ ውጤት የሚያሳይ ምርመራ ከአገራቸው ይዘው እንዲመጡ በመደረጉ ምክንያት በቫይረሱ የሚያዙ ተሳታፊዎችን ቁጥር መቀነስ እንዳስቻለም ዶ/ር ሚኪያስ አክለዋል፡፡
በየዕለቱ ወደ አፍሪካ ህብረት በሚገቡ ተሰብሳቢዎች ላይ ከሚወሰደው ምርመራ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር ከ0 ነጥብ 5 በመቶ በታች መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ሚኪያስ በቀን ከሶስት ሺህ በላይ ናሙናዎች በአፍሪካ ህብረት ግቢ ውስጥ በመመርመር ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
እንግዶች ወደ መሰብሰቢያ አዳራሾች ከመግባታቸው በፊት በአፍሪካ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል ባለሙያዎች በሚያደርጉት ቁጥጥር ከቫይረሱ ነጻ የሖኑበትን ማስረጃ ካረጋገጠ በኋላ N95 የተሰኘውን የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ወይም ማስክ በማደል ወደ ስብሰባ ቦታዎች እንዲገቡ በመደረግ ላይ ነው፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ምርመራ ባለፈም እንግዶች የጤና እክል ቢያጋጥማቸው የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ጊዜያዊ የህክምና ማዕከል ተቋቁሟል፣ አምስት አምቡላንስም ከበቂ የህክምና ባለሙያዎች ጋር ዝግጁ መሆናቸውን ዶ/ር ሚኪያስ አክለዋል፡፡
እንግዶች ለስብሰባው ወደ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ሲመጡ በየዕለቱ የሚደረገውን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለማቀላጠፍ የምርመራ ውጤት በኢሜላቸው እንዲደርሳቸው በመደረግ ላይ መሆኑንም ዓልዓይን ታዝቧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ናሙና ከተሰጠ በኋላ የምርመራ ውጤት በኢሜይል ከ10 እስከ 15 ደቂቃዎች ውስጥ እንደሚደርስም የአልዓይን ጋዜጠኞች የሕብረቱን ጉባኤ ለመዘገብ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ባካሄዱት ምርመራ ወቅት አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ስራን ለማቀላጠፍ በሆቴሎች እና በቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡