35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬ በህብረቱ መዲና አዲስ አበባ ተጀምሯል
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬ በህብረቱ መዲና አዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡
በጉባዔው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ ለዚህም ከትናንት ከትናንት በስቲያም ጀምሮ መሪዎቹ ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ለ40ኛው የህብረቱ የስራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ በሚል ከሰሞኑ ወደ አዲስ አበባ የገቡም አሉ፡፡
“የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማፋጠን” በሚል መሪ ቃል ዛሬና ነገ በሚካሄደው በዚህ የመሪዎች ጉባዔ ጥቂት የማይባሉ መሪዎች አይገኙም፡፡
በጉባዔው ከማይገኙ ሃገራት መሪዎች መካከል በዋናነት የምዕራብ፣ የመካከለኛው እና የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና መሪዎች ይገኙበታል፡፡
በጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ባሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት መገባደጃ በወሰደው እርምጃ ስልጣን መያዙን ተከትሎ ከህብረቱ የትኞቹም ዐይነት እንቅስቃሴዎች ታግዷል፡፡ ይህ በህብረቱ ጉባዔዎች አለመሳተፍ ጭምር የሚያካትት ነው፡፡
በዚህም ያቋቋሙት ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት መሪ የሆኑት የሱዳን ወታደራዊ ጄነራሎች በዚህ ጉባዔ አይሳተፉም፡፡
ልክ እንደ ሱዳን ሁሉ ጥቂት የማይባሉ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት ተመሳሳይ እጣ ፋንታ ገጥሟቸዋል፡፡
መፈንቅለ መንግስት ተደጋግሞ በስተዋለበት በዚህ የአፍሪካ ቀጣና ጥቂት በማይባሉ ሃገራት የመንግስታት ለውጦች ተደርገዋል፡፡
ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ጊኒ እና ቻድ ለዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በቅርቡ በጊኒ ቢሳው እና በኒጀር የተደረጉ የመንግስት ለውጥ ሙከራዎች መክሸፋቸው መነገሩም ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎ ዴሞክራሲያዊ ተብለው ከሚጠሩ ምርጫን መሰል አካሄዶች ውጭ የመንግስት ለውጥ ያደረጉ ሃገራት መሪዎች ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ እንደሚወያይ በሚጠበቀው ጉባዔ ላይ አይገኙም፡፡
ህብረቱ አግዷቸው በጉባዔው ካልተገኙ ከእነዚህ ሃገራት መሪዎች ውጭ በራሳቸው ፈቃድ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ተወካዮቻቸውን ልከው በጉባዔው ያልተገኙ ሌሎች የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎችም አሉ፡፡
በቻይና ዊንተር ኦሎምፒክ መክፈቻ ላይ ለመገኘት ወደ ቤጂንግ ያቀኑት የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲን ጨምሮ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የታንዛኒ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ስሉህ እንዲሁም የርዋንዳውን ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እና ሌሎችም ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡