በሴኔጋል ሆስፒታል በደረሰ የእሳት አደጋ የ11 ጨቅላ ህጻናት ህይወት አለፈ
ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ለህጻናቱ እናቶችና ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል
አደጋው በርካቶችን ያስቆጣ ሲሆን ኃላፊነታቸውን ያለውተወጡ ሰዎችም ተጠያቂ እንዲደረጉ ተጠይቋል
በሴኔጋል ታይቩን ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የ11 ጨቅላ ህጻናት ህይወት ማለፉን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የእሳት አደጋው በሆስፒታሉ የጨቅላ ህጻናት ህክምና ክትትል ክፍል ውስጥ የደረሰ ሲሆን፤ የሶስት ህጻናትን ህይወት መታደግ እንደተቻለ የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሴኔጋል ጤና ሚኒስትር በአብዶላይ ዲዮፍ ሳር በሰጡት አስተያየት፤ የእሳት አደጋው የተነሳው ከኤሌክቲሪክ ጋር በተያያዘ ችግር እንደሆነ በመግለጽ በዘለለ ሌላ አስተያየት ተቆጥበዋል።
“አደጋው በአጣም አስደንጋጭ እና አሳዛኝ” ነው ያሉት የጤና ሚኒስትሩ፤ በአደጋው ዙሪያ ምርመራዎች እየተካሄዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል አደጋውን ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ታይቩን ከተማ በሚገኘው ማሜ አበዱ አዚዝ ዳባከህ ሆስፒታል የደረሰወን እና የ11 ጨቅላ ህጻናት ህይወት የቀጠፈውን የእሳት አደጋ ዜና በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ሆኜ ነው የሰማሁት” ብለዋል።
በአንጎላ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳነቱ “በእሳት አደጋው ጨቅላ ልጆቻቸውን ላጡ እናቶች እና ለቤተሰቦቻቸው፣ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁ” ብለዋል።
የእሳት አደጋው በርካታ ሴኔጋላውያንን ያስቆጣ ሲሆን፤ ኃላፊነታቸውን ያለውተወጡ ሰዎችም ተጠያቂ እንዲደረጉ በርካቶች እየጠየቁ ይገኛሉ።