በሕንድ የኮሮና ክትባት በሚመረትበት ተቋም ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 5 ሰዎች ሞቱ
ምንም እንኳን አደጋው ቢደርስም ክትባቱን የማምረቱ ስራ ይቀጥላል ተብሏል
የእሳት አደጋው የተከሰተው በዓለም ትልቁ በሆነው የክትባት አምራች ተቋም ላይ ነው
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኦክስፎርድ/አስትራዜኔካ የኮቪድ-19 ክትባት ‘ዶዞችን’ በማምረት ላይ በሚገኘው የህንድ ተቋም ላይ ትናንት በደረሰ የእሳት አደጋ የ 5 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
በፑና ከተማ በሚገኘው እና ገና ግንባታው ባላለቀው የተቋሙ ህንጻ ላይ ትናንት ከሰዓት በኋላ ነበር አደጋው የደረሰው፡፡ እሳቱ ምሽት ላይ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን መንስኤው እስካሁን እንዳልታወቀ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የተቋሙ ባለቤት እና ዋና ስራ አስፈጻሚ አዳር ፖናዋላ በሰጡት መግለጫ “ዛሬ ለሴረም ተቋም ሰራተኞች ሁሉ አሳዛኝ ቀን ነው፡፡ በእሳት አደጋው የሰዎችን ህይወት አጥተናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አደጋው የደረሰው በግምባታ ላይ በሚገኘው የህንጻው ክፍል ሲሆን ለሟች ቤተሰቦች በነፍስወከፍ 34 ሺ ዶላር እንደሚሰጣቸውም ነው የገለጹት፡፡
ሴረም የተሰኘው አደጋው የደረሰበት ተቋም ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና አስትራዜኔካ ጋር በመተባበር ኮቪሺልድ የተሰኘ የኮሮናቫይረስ ክትባት የሚያመርት ነው፡፡ ተቋሙ በወር ከ 50-60 ሚሊዮን የክትባት ‘ዶዞችን’ እንደሚያመርት ባለፈው ታህሳስ አስታውቆ ነበር፡፡ በጥር እና የካቲት ወራት ደግሞ የማምረት አቅሙን በወር ወደ 100 ሚሊዮን ‘ዶዝ’ እንደሚያደርስ ገልጿል፡፡ በዚህም ተቋሙ ከሕንድ ባለፈ ለሌሎች ታዳጊ ሀገራትም ክትባቱን የማድረስ እቅድ አለው፡፡
ከህንጻው ስድስት ወለሎች የተወሰኑት ጉዳት ቢደርስባቸውም በኮቪሺልድ ክትባት ምርት ላይ ጉዳት አለመድረሱን እና ምርቱም እንደሚቀጥል ዋና ስራ አስፈጻሚው አዳር ፖናዋላ ገልጸዋል፡፡
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በትዊተር ገጻቸው ፣ በአደጋው የሰዎች ህይወት በማለፉ ሀዘናቸውን ገልጸዋል፡፡